ግለሰብ በህግ የማህበረሰብ ውክልና ሳይኖረው ከመሬት ተነስቶ አፉን ቢከፍት ተቀባይነት የለውም። ውክልና ቢኖረውም እንኳን አፈንግጦና ስድ አድጎ የሚናገር ግለሰብ ንግግር ዠማውን አይወክልም።

ግን ደግሞ አንዳንዴ በእኩይ አስተሳሰብ የተሳከረ፤ በልሙጥ አተያይ ደዌ የተመታ ቡድን ሃሳቡ በግለሰቦች ቢራመድም የሃሳቡ ባለቤት ግለሰብ ብቻ ነው ብሎ ማሰብና መደምደም ግን የዋህነት ይሆናል።
ምን ለማለት ነው ድብቅ አጀንዳ ብብታቸው ስር ደብቀው የራሳቸውን መርዝ ሃሳብ የማህበረሰብ መልክና ቀለም አስመስሎና ቀብቶ የግጭት ድግስ ደጋሾችን እና ከበሮ ደላቂዎችን ለይቶ ማጋለጥ እንዲሁም ወደ ፍትህ አደባባይ ማቅረቡ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባዋል።
የዚህ የሸፍጥ ፓለቲካ ስፓንሰሮች አወቃቀር እና ሰንሰለት ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከመንደር እስከ አረብ፤ ከተከፋይ ጋዜጠኛ እስከ ዘውገኛ ሚድያ፤ ከቅዱሳን እስከ እርኩሳን፤ ከከሰረ ፓለቲከኛ እስከ ሰፈር አርበኛ፤ ከአክቲቪስት በ”አርቲስት” አድርጎ እስከ አትሊስት፤ ከዳይፐር እስከ “ሚኒስተር”… እየተናበበ ኦኬስትሬት የሚያደርግ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ብሎም ፀረ-ኦሮሙማ ወይም ፀረ-አፋሩማ አልያም ፀረ-ሱማሉማ ጅምላ ጨራሽ ጨፍላቂ አስተሳሰብ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ተግባር ነው።
ማንኛውም አካል ቢሆን የማንኛውንም ማህበረሰብን ክብር የሚነኩ፤ ስምና ዝናን የሚያጠለሹ አስተሳሰቦች በማራመድ ማህበራዊ መሠረት እንዳላቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ ስህተት ሲሆን ችግሩን በወቅቱ አለማረቅ ደግሞ ሌላኛው ፈተና ይሆናል።
ይሄ ሁሉ ጥፋት በየአከባቢው ሲደርስ በየደረጃው ያለው የመንግስት አካል ምን እየጠበቀ ነበር? አመራሩ ከትላንቱ ጥፋት ለምን ዛሬ መማር ተሳነው? የሁኔታ ግምገማ በማድረግ ቅድመዝግጅት ማድረግ ለምን አልተሞከረም? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ስናይ በየደረጃው ያለ የመንግስት አካል የአመራር ክህሎቱና ሚናው ያነሰ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በአንድም በሌላም የችግሩ ሰለባ መሆኑን የችግሩን አሳሳቢነት ያመላክታል።የዚህ አይነቱ ማህበራዊ መናጋትን የሚፈጥሩ ተግባራት አፅንኦት ተሰጥቷቸው በአግባቡ ካልተያዘ በስተቀር ማህበረሰቦች በጋራ ለዘመናት የገነቡትን እሴት ይንዳል። አብሮ መኖርን ጥያቄ ውስጥ ይከታል።
መቻቻልን እና ግንኙነትንም ያሻክራል። ማህበራዊ መስተጋብርም ያውካል።በሌላ መልኩ በደልን ለመቃወምና ለማስተጋባት ፍትህን ፈልጎ አደባባይ ላይ መውጣት ተገቢም፣ መብትም ሆኖ ሳለ በተቃራኒው ሌላ በደል መፈፀም ግን በህግም፣ በዕምነትም፣ በሞራልም ሆነ በጤናማ ማህበራዊ መስተጋብር ተቀባይነት የለውም።ካለፉት ሶስት አመታት ተለዋዋጭና ተከታታይ ተሞክሯችን እንደዚህ አይነት የአደባባይ ላይ በደሎች የተበዳዩን ወገን ስሜታዊነት ሆን ብሎ በማነሳሳ እና እንደ መልካም የችግር መፍጠርያ አጋጣሚ በመጠቀም ሃገርን ለማተራመስ ያለመ የቁማር ፓለቲካ ኘሮጀክት መሆኑንም መረዳት ተገቢ ይሆናል።
ሲጠቃለል ዜጎችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መጣር የዘውገኞች እና የአዛኝ ቅቤ አንጓቾችና አግድም አደግ እንክርዳዶች ሴራ ሲሆን የኢትዮጵያን ልማት በበጎ ጎኑ የማይመለከቱ የውጪ ሃይሎች ጭምር የትግል ስልት መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለጌ በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ አለ። “የራስን እብድ እና የራስን ገንዘብ ባለቤቱ ነው የሚያስረው” የሚባለውን ብሂል ማጤን፤ ባለጌንም ልጅ ቤተሰቡ ሊመክረውና ሊቀጣው እንደሚገባ ማስታወሱም ተገቢ ነው። ኢትዮጵያን የሚወድ እና የሚያከብር ሁሉ በማህበረሰቦች ላይ የሚሰነዘሩ እኩይ አስተሳሰቦችን እና ተግባሮችን አጥብቆ ማውገዝ እና ማጋለጥ ይገባል።
ማስታወሻ፦ ኦሮሙማ ኦሮሞነትን ያለምንም ልዩነት በእኩል የሚጋሩት የወል/የጋራ መጠርያ ስም ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ እሴቶች ጭምር የሚገልፅ ፓኬጅ ነው።
በላይ ባይሳ ሚያዝያ 12/2013 ዓ.ም – ይህ ነጻ አስተያየት የጸሃፊውን ሃሳብ ብቻ የሚወክል ነው።
- “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳየትህነግ ቃል አቀባይ በመሆን ጦርነቱን በፕሮፓጋንዳ ሲያቀጣጥሉት የነበሩት አቶ ጌታቸው… Read more: “ ንስሃ ገብቻለሁ እስካሁን የዋሸሁት ይበቃኛል ፤ ሲያፈገፍጉ የተረሸኑ ታጋዮች አሉ ” አቶ ጌታቸው ረዳ
- ለምህላቸው ከሚኖሩት መካከል – ሰርጉን ጥሎ ነብስ የታደገው ሐኪምሰሞኑን ከሚሰማው የሐኪሞች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ጎን ለጎን የተሰማው ዜና… Read more: ለምህላቸው ከሚኖሩት መካከል – ሰርጉን ጥሎ ነብስ የታደገው ሐኪም
- ፕሮፌሰር ክንድያ የደብረፅዮንን ቡድን “ካለፈ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ” አሉት፤ ፋኖ የደቦ አመራር ሰየመበጦርነቱ ወቅት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ፕሮፌሰር ክንድያ ገብረህይወት “የደብረፅዮን ቡድን… Read more: ፕሮፌሰር ክንድያ የደብረፅዮንን ቡድን “ካለፈ ስህተቱ የማይማር ተቸካይ ” አሉት፤ ፋኖ የደቦ አመራር ሰየመ