በተመረጡ ቦታዎች፣ የግልና የመንግስት ተቋማት ላይ ቦንብ ማፈንዳቱን ፋኖ አስታወቀ። ይህን ያስታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የአባይ ድልድይን ለመመረቅ ወደ ባህር ዳር እንዳይመጡ ለ”ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ” በሚል በተለያዩ ቦታዎች ቦንብ ማፈንዳቱን ሃላፊነት ወስዶ ባስታወቀበት ወቅት ነው። ድልድዩ ሲመረቅ አብይ አህመድ ” መገዳደል ይብቃ ” ጥሪ አቅርበዋል።
ፋና ሙሉ ሰው እንዳሉት በተመረጡ የግልና የመንግስት ተቋማት ላይ ቦንብ የተጣለው አብይ እንዳይመጡ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው። ስለደረሰው ጉዳት መረጃ እንዳልደረሳቸው የጠቀሱት እኚሁ ሰው ለአቶ መሳይ መኮንን ዩቲዩብ እንዳሉት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ላይ ቦንብ ተጥሏል። ተቋሙ ግን ዜናውን እያሰራቸና ህንሳው ላይም ሆነ በአካባቢው ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ተመልክቷል።
ግንባታውን ከፌደራል መንግስት በተመደበ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በጀት ዓለም አቀፉ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሲሲሲ የተገነባው፣ የቱርኩ ቦቴክና ሀገር በቀሉ ስታዲያ ኢንጅነሪንግ የግንባታውን የቁጥጥር እና የማማከር ሥራ በጥምረት ያከናወኑለት ግድቡ እጅግ እንደሆነ ተመልክቷል። ህዝብም ደስታውን ገልጿል።
ግንባታውን አስመልክቶ ድርጅታቸው የያዘውን አቋም በአቶ መሳይ ያልተጠይቁት ፋኖ ሙሉ ሰው፣ ወደ ምረቃው በሚያመሩና በሚሳተፉ ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወስዱ አመልክተዋል።
የዓባይ ወንዝ ድልድይ የባሕር ዳር ከተማን በመሐል አቋርጦ የሚያልፍ ሲኾን፣ በተንጠልጣይ ገመዶቹ እና ምሶሶዎቹ ላይ ዘመናዊ መብራት የተገጠመለት በመኾኑ ለአካባቢው ልዩ ድምቅት ከመስጠቱም ባለፈ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያሳልጥ እንደሆነ በስፋት መገለጹን ተከትሎ “ሁሉም ንብረቴ ብሎ ሊጠብቀው ይጋባል” በሚል ነዋሪዎች አስተያየት ሲሰጡ በምስል ታይተዋል።
በሀገሪቱ ታሪክ በዓይነቱ ልዩ የኾነው ይኽ ድልድይ 380 ሜትር ርዝማኔ እና 43 ሜትር የጎን ስፋት አለው። በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን በግራ እና በቀኝ ያስተናግዳል። በግራና ቀኝ የብስክሌተኞች መተላለፊያ ሰፊ ኮሪዶር አለው። አምስት ሜትር የእግረኛ መንገድ አካትቷል። እያንዳንዱ የድልድዩ ገመድ አቃፊ ማማዎች ቁመት 27 ሜትር ከፍታ አላቸው። ከውኃና ከመሬት በታች እስከ 24 ሜትር ጥልቀት ባላቸው በርካታ ፓይሎች የተዋቀረ ነው፡፡ ይህ ድልድይ ሲመረቅ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልታኖች፣ አመራሮች፣ የብልጽግና ሃላፊዎች፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ነዋሪዎች፣ የክልሉ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ምርቃቱ ከተከናወነ በሁዋላ ፋኖ እንዳለው የዲሽቃ ጥቃት ተሞክሯል። ምርቃቱ ከሚደረግበት የአባይ ድልድይ ሰባና መቶ ሃምሳ ሜትር ላይ መውደቁን ገልጸዋል። ዜናውን የሰሙ “ሰባ ሜትር ማለት ድልድዩ ላይ ወደቀ ማለት ነው” ሲሉ ተደምተዋል። ይህ ቢሆን የምረቃው ስነ ስርዓት ሊከናወን አይችልም ነበር።
ከምረቃው በፊት በጎርጎራ አዳራቸውን አድርገው የነበሩት አብይ አህመድ ጎርጎራን የመስለ ልዩ መስ ዕብ ያለው መዝናኛ አይተው እንደማያውቁ አብረዋቸው ከነበሩ ባልስልጣኖች ጋር ማውሳታቸውን ጠቅሰው ” ሂዱና ጎብኙት” ብለዋል። አያይዘውም የአባይ ድልድይ ቀታዩን ትውልድ ታሳቢ አድርጎ የተሰራ በመሆኑ ፓርቲያቸው አሻግሮ የሚያይ ለመሆኑ ማሳያ አድርገው ፡ እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉ ባልደረቦቻቸውን፣ የለፉትንና ለስራው መሳካት የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል።
“ገና ብዙ እንሰራለን” ያሉት አብይ አህመድ ለባህር ዳር ከንቲባ ” ከንቲባነት ያልፋል ባህር ዳር ትቀጥላለች” ሲሉ ለታሪክና ለትውልድ የሚታወስ ስራ እንዲሰሩ አሳስበዋል። አደራ ብለዋል። “ባህር ዳይ የታደለች ከተማ ናት ግን መሪ አላገነችም” ሲሉ ጥሩ መሪ እንዲሆኑ መክረዋል።
ህዝቡ አንድ ሆኖ ለልማት እንዲነሳ ጥሪ ያቀረቡት አብይ አሕመድ ለክልሉን መንግስት “ተባበሩን” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። ብዙ የሚገነባና የሚፈርስ ድልድይ መኖሩን ጠቁመዋል። የሃሰት ትርክት ኢትዮጵያዊያንን ዋጋ እንዳስከፍላቸው ጠቅሰው፣ ይህን የሃሰት ትርክት ድልድይ ለማፍረስና አዲስ አንድ የሚያደርግ ትርክት ለመገንባት ጉዞ መጀመሩን ጠቁመው የክልሉ አስተዳደር በዚህ ረገድ ከፌደራል መንግስት ጋር አብሮ እንዲሰራ ጠይቀዋል። አደራ ብለዋል።
“ስለ አማራ መብት እንቆረቆራለን በሚል ጫካ የገባችሁ ወንድሞች ከክልላችሁ መንግስት ጋር አብራችሁ እንድትሰሩ ጥሪ አቀርባለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በንግግራቸው ማብቂያ ላይ ተናግረዋል።
ስለ አማራ ዲሞክራሲ የሚታገል ማንኛውም ግለሰብ እና ቡድን ሰክኖ በማሰብ ሕዝቡን እና ክልሉን መጥቀም በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
ስለ አማራ መብት፣ ልማት እና ዲሞክራሲ እንቆረቆራለን በሚል ጫካ የገባችሁ ወንድሞች ለዚህ ግዜው ባለመሆኑ ከክልላችሁ መንግስት ጋር አብራችሁ ልትሰሩ ይገባል፤ ሞት ይበቃል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ብልጽግና በኢትዮጵያ ልክ የሚሰራ፣ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚመጥን ስራ የሚሰራና በቃሉ የሚገኝ ፓርቲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ብልጽግናን እንመኛለን ስንል በንግግር ያልተገነዘቡን ሰዎች በዚህ ድልድይ ብልጽግና ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲረዱ እፈልጋለሁ ብለዋል።
የብልጽግና ራዕይና ተልእኮ ያሳከውን ድልድይ ላይ ቆሜ ይህ ንግግር በማድረጌ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የዓባይ ወንዝ ድልድይ በሀገሪቱ ግዙፍ ከሚባሉ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የሚገባትን፣ የአማራ ሕዝብ የሚገባውን፣ ለባሕር ዳርም ውበት የሚመጥን ታላቁን ሥራ በጋራ ለማስመረቅ በቅተናል ሲሉም ተናግረዋል።
በሕዝቦች መካከል በተፈጠሩ አልባሌ ትርክቶች ምክንያት እየላላ ያለውን ትስስር ሊያጠናክር የሚችል የትርክት ድልድይ መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡
እንደመንግስት ሁለት ድልድይ ለመገንባት እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያው ልማትን የሚያሳልጥ ድልድይ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ህዝብን የሚለያይ ግድግዳ በማፍረስ የአንድነት ድልድይ መገንባት ነው ብለዋል፡፡
ይህ ሁለት ዓይነት ድልድይ ኢትዮጵያን በርቀት ያሻግራል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን የሚመጥን ድልድይ በውቧ ባህር ዳር ከተማ ማስቀመጥ ለቻሉ ባለሙያዎች እና መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓባይ ድልድይ ምረቃ ላይ ለእናቶች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትም አስተለልፈዋል፡፡