ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በደቡብ ትግራይ በራያ አዘቦ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው ሃላፊ ተዘራ ጌታሁን አስታወቁ። ጥቃቱን ያደረሱት ትግራይ ክልልን ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስነው አቅጣጫ ዘልቀው የገቡ የአፋር ተወላጆች ናቸው ተብሏል። የአፋር ክልል ያለው ነገር የለም። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጥቃት ፈጻሚዎቹን የፌደራል መንግስትና የአፋር ክልል ለይተው በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ ጠይቋል። በሌላ መልኩ የትግራይ ሃይሎች ጥቃት ማድረሳቸው ተሰምቷል።
ጥቃቱ የተፈጸመው እና ንጹሃኑ የተገደሉት “ኢሊጎባ” ተብላ በምትጠራ መንደር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ሰኞ ሌሊት በተኙበት ነው ያሉት ሃላፊው ጥቃት አድራሾቹ “የአፋር ታጣቂዎች ናቸው፣ በጥቃቱም የአስራ አንድ ዓመት ህጻንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ከሰጡት መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ጥቃቱን ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ “በራያ አዘቦ ወረዳ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ ወገኖቻችን በግፍ ተጨፍጭፈው ሞተዋል” ብሏል።
“ይህንን ዘግናኝ ወንጀል የፈፀሙ ኣካላት ከአፋር አከባቢ የመጡ ናቸው” ሲል በመግለጽ ማንነታቸው በሚመለከት የትግራይ ክልል ግዝያዊ መስተዳድር ጥብቅ ክትትል እያደረገ ይገኛል ብሏል።

ወንጀለኞችን ለመለየትና ለመያዝ የሚደረግ ጥረትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና የደረስሰበትን ሁኔታም በየግዜው ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ፌደራል ፖሊስም ወንጀለኞችን ተከታትለው በመያዝ ወንጀል ወደ ፈፀሙበት አከባቢ መጥተው ይዳኙ ዘንድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
የራያ ዓዘቦ ወረዳ ህዝብና አስተዳደር ሁኔታውን ለማረጋጋት እና ለመቆጣጠር ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት የሚበረታታ ነው ሲል የክልሉ መንግስት በኮሙዩኒኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ አወድሷል። የወረዳው ሃላፊ ተዘራ ጌታሁን የጥቃቱ ዋነኛ መነሻ እየተጣራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሃላፊው ጉዳዩ ወደ ሌላ ግጭት እንዳያመራ ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል። አሁንም ምሽግ እየተቆፈረ እንደሆነ ለቪኦኤ ገልጸዋል።
ይህ በንዲህ እንዳለ የትግራይ ሃይሎች ሶስት የአፋር ቀበሌዎችን አልፈው መግባታቸው ተሰምቷል። በተፈጠረው ግጭትም ከአፋር የጸጥታ ሃይሎችና ከትግራይ በኩል ጉዳት መድረሱ ተሰምቷሎል። የትግራይ ሃይል አባላት ሆነው የሞቱና የቆሰሉ ወደ መቀለና መሆኒ ሲጓጓዙ ማየታቸውን ምስክሮች ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በሁለቱም ወገን የደርሰውን ጉዳት በዝርዝር አላስረዱም።
ይህንኑ ተከትሎ ከአፋር ወገኖች በኩል “የትግራይም ሆነ የአፋር ህዝብ ጦርነት ስልችቶታል ” በሚል የትግራይ ሃይሎች ወደ አፋር ክልል ገብተው እያካሄዱ ያሉትን ግጭት ከማባባስ እንዲቆጠቡ እያሳሰቡ ነው። መንግስት ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን ያለው ነገር የለም። የአፋር ክልልም ለጊዜው ምላሽ አልሰጠም።