በመሰረታዊ እሳቤው ላይ ቅሬታ የማይነሳበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የከተማ አስተዳደርና ክልላዊ የምክክር ምዕራፉን ነገ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚጀምር ኮሚሽኑ አስታውቋል። ኮሚሽኑ ብረት ካነሱ ሃይሎች ጋር ንግግር መጀመሩም ታውቋል።
እንደ ዶክተር በድሉ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች “በብሔራዊ ምክክሩ በጥቃቅን ጉዳዮች ከመነታረክ ይልቅ በወሳኝ ጉዳዮች ተወያይቶ መታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የጎሳ ፖለቲካ በአግባቡ ካለመያዙ የተነሳ የጋራ እሴቶች በእጅጉ ተሸርሽረዋል። በልዩነት ውስጥ የአንድነት መንፈስ ሊጠናከር ሲገባው ግለኝነት ጎልቶ በመውጣቱ ምክንያት የጋራ ጉዳዮች አደጋ ላይ ወድቀዋል” ሲሉ በጥቃቅን ጉዳዮች ከመነታረክ ይልቅ ያለመግባባት መነሻ በሆኑ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለመታረቅ መዘጋጀት እንደሚገባው ያሳሰቡት አንኳር ነጥብ ይታወሳል።
ገና መቋቋሙ ይፋ በሆነበት ሰአታት ውስጥ “እንደሚፈርስ አስጠነቀ” በሚል ዜና ህዝብ ጆሮ እንዲደርስ የተደረገው አገራዊ ኮሚሽኑ፣ ሻዕቢያን ጨምሮ የኮሚሽኑ አካሄድና ውጤቱ የገባቸው የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ኮሚሽኑ የህዝብ አመኔታን እንዲያጣ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። በተለይም የዛሬው የትግራይ ክልል ጊዚያዊ መሪ የሆኑት አቶ ጌታቸውና የትህነግ ደጋፊዎች በስፋት ዘመቻ ከፍተውበት እንደነበርም አይረሳም።
በአገራችን የፖለቲካ ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረጉ ውስን ንግግሮች ወይም ድርድሮች በውጭ አገር ጣልቃ ገብነት የተከናወኑ በመሆናቸው ያንን አስወግዶ በአገር ልጅ ለመዳኘት ታስቦ የተቋቋመው ይህ አገራዊ ኮሚሽን ኢትዮጵያን እየናጡ የኖሩትን ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደ አግባቡ በተቀመጡ አጋብቦች ለመቋጨት ስያደርግ የነበረውን ቅድመ ሁኔታ አጠናቆ የምክክር መደረኩን በአዲስ አበባ እንደሚጀምር ታውቋል።
ለሠባት ቀናት በሚቆየው በዚህ የምክክር ምዕራፍ ላይ በቀዳሚነት ለምክክሩ የሚቀርቡ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የአጀንዳ ሀሳቦችን እንደሚያመጡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ(ዶ/ር) ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የሚነሱ ማንኛውንም አጀንዳዎች ለማስተናገድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ነው ኮሚሽነሩ አምልክተዋል። በምክክሩ ላይ የሚገኙት ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ አሰባስበውና አደራጅተው የመፍትሔ ሀሳቦችንም በዚሁ ምዕራፍ ያቀርባሉ ነው የተባለው።
በተጨማሪም የሂደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክር አጠቃላይ ጉባኤ ተሳታፊ የሚሆኑ አጀንዳዎችንና ተወካዮቻቸውን እንደሚመርጡ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ምክክሩ ሁሉንም ያካተተ እንዲሁን በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። ጥሪውን በገሃድ ያጣጣሉ፣ እንደማይቀበሉ የጠየቁ አሉ። ይሁን እንጂ ለንግግሩ ቀናነት ሲባል ስምና ማንነት ሳይጠቀስ ኮሚሽኑ ብረት ካነሱ ሃይሎች ጋር ውይይት መጀመሩን አመልክቷል።
የስብሰባው ሥነ-ስርዓቶች
ይህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አካታች፣ አሳታፊና ሃሳቦች በግልጽ የሚንሸራሸሩበት ሂደት እንዲሆን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ባለድርሻ አካላትን ወክለው የሚሳተፉ ተሳታፊዎች የሚከተሉትን የስብሰባ ሥነ-ስርዓቶች ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡
1. ማንኛውም ተሳታፊ በነጻነት ሀሳቡን የመግለጽ መብት አለው።ሆኖም ተሳታፊዎች ከጥላቻ፣ ከአዋራጅ እና ከተንኳሽ ንግግሮችመቆጠብ፤
2. በምክክሩ ጊዜ መደማመጥን ከሚያውኩ፣ ሁከትን ከሚፈጥሩ እና መረጋጋትን ከሚነፍጉ ድርጊቶች እና ንግግሮች መቆጠብ፤
3. በጽሁፍ፣ በምልክት ወይም በድምጽ የጎንዮሽ ንግግር አለማድረግና ከተሳታፊዎች የሚቀርበውን ሃሳብ በአክብሮትና በጥሞና ማዳመጥ፤
4. እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚሰጠውን ሃሳብና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማክበር፣ በቅንነትና በታጋሽነት ማዳመጥ ፤
5. ሌላው ተሳታፊ ያቀረበውን ሃሳብ የመደገፍ ወይም የመቃወም ሁኔታ ሲኖር የሌሎች ተሳታፊዎችን መብት በሚያከብር መልኩ ማቅረብ፣
6. ተሳታፊው እድል ተሰጥቶት ሃሳቡን በመግለጽ ሂደት ላይ እያለ በማንኛውም ሁኔታ ያለማቋረጥ፤
7. የሰውን ክብር ከሚነኩ ነቀፌታዎች፣ ዘለፋዎች፣ ስብዕናን ከሚነኩ ንግግሮችና ድርጊቶች መቆጠብ፤
8. ሰዎች በሚያቀርቡት ሃሳብ እና አስተሳሰብ ባይስማሙ እንኳ ሃሳባቸውን እና አስተሳሰባቸውን ማክበር፤
9. የሚሰጠው ሀሳብ በቅን ልቦና ላይ የተመሠረተ ሆኖ ከውይይቱ አጀንዳ ጋር አግባብነት ያለው አጭር፣ ግልጽ ያልተደጋገመ እና የተፈቀደውን ጊዜ ባከበረ መልኩ መግለጽ፤
10. በሂደቱ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቅ ናቸው፡፡
እነዚህን የስብሰባ መሠረታዊ ሥነ-ስርዓቶች ተግባራዊ በማድረግ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የበኩልዎን ኋላፊነት ይወጡ።