የሕወሓት ታጣቂዎች ሀብት ንብረት እየዘረፉ ወደ ትግራይ እየጫኑ ነው
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ነዋሪዎች በሕወሓት ዳግም ወረራ ከተፈጸመባቸው ሰነባብተዋል፡፡ ሕወሓት የሰላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ በአማራ ክልል ወረራ መፈጸሙን የአማራ ክልል መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ መንግሥት ታጣቂዎች በወረራ ከያዙት አካባቢ ለቀው እንዲወጡም አሳስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁንም የሕወሓት ታጣቂዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ስቃዩን እያበዙበት መኾናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በወረራው ምክንያትም ብዙዎቸ ተፈናቅለዋል፤ ሃብት እና ንብረታቸውንም አጥተዋል፡፡
ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን የተውነው የአላማጣ ከተማ ነዋሪ በአላማጣ ገጠር ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች የሕወሓት ታጣቂዎች ሀብት ንብረት እየዘረፉ ወደ ትግራይ እየጫኑ ነው ይላሉ፡፡ አርሶ አደሮች እርሻ በሚያርሱበት በዚህ ወቅት ከቀያቸው እየተፈናቀሉ በመከራ ውስጥ ናቸው ይላሉ፡፡
በአላማጣ ከተማም በሌሊት የተደራጀ ዘረፋ እንደሚፈጽሙ አንስተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በአስቸጋሪ የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች በአካባቢው ከዛሬ ነገ ይወጣሉ እየተባለ ለሕዝብ ቢነገርም እስካሁን ድረስ እየዘረፉ፣ እያወደሙ፣ ማኅበረሰብ እያሰቃዩ እና እያፈናቀሉ ተቀምጠዋል ነው የሚሉት፡፡
ሁሉም ሊረዳን የምንፈልገው አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነን ብለዋል፡፡ የእኛ ፍላጎታችን ማንነታችን ተከብሮ፣ ሰላም ተረጋግጦ፣ በሰላም እየሠሩ መኖር ነው፤ የራያ ሕዝብ ነጻነት ይፈልጋል፤ መንግሥት ስጋት የኾኑንን አካላት እንዲያስወጣልን እንጠይቃለን፤ የራያ ሕዝብ የሚፈልገው ማንነቱ ተረጋግጦለት መኖር ነው፣ መንግሥት የሰላም ስምምነቱን ባለው ልክ እንዲፈጸም እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የራያ ሕዝብ አማራነቱን ይዞ፣ በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ ለመኖር ነው ፍላጎቱ፤ መላው ኢትዮጵያውያን፣ መላው የዓለም ማኅበረሰብ ጥያቄያችን እንዲያውቅልን፣ በደላችን እንዲረዳልን እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ከራያ ጎን ሕዝብ ጎን እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሌላኛው የአላማጣ ከተማ ነዋሪ በገጠር አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ግፍና በደል እየደረሰበት ነው፤ ሰበቦች እየተፈለጉ ሃብት እየተዘረፈ ነው፤ ነዋሪዎች እየተደበደቡ ላም እና በሬዎቻቸው እየተነዱ እየታረዱ ነው፤ አማራ ነን ስላልን ብቻ ግፍ እየተፈጸመብን ነው ይላሉ፡፡ ወደ ከተማ የገቡት ታጣቂዎች ደግሞ ቀን ቀን መሳሪያቸውን ደብቀው በከተማዋ ሲዘዋወሩ ይውላሉ፤ ሌሊት መሳሪያቸውን አንስተው ሲዘርፉ፣ ሲያወድሙ ያድራሉ ነው ያሉት፡፡ ሐሰተኛ መታወቂያ እየተሰጣቸው ሕገወጥ ሰዎች አካባቢውን ወረውታልም ብለዋል፡፡
በራያ ውስጥ የአማራ ማንነት መገለጫዎች የኾኑ ምልክቶች እና ለታሪክ የሚቀመጡ ማንኛውንም ጉዳዮች እያፈረሱ ነውም ይላሉ፡፡
የራያ ሕዝብ በማንነቱ አይደራደርም፣ ማንነቴን ያስመልስልኛል ብሎ መንግሥትን አምኖ ተቀምጧል፤ ከሕወሓት ቡድን ነጻ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ የማንነቱ ጥያቄ በሕግ እንዲጸድቅለት ፍላጎቱን በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰልፎች ጠይቋል፤ ይሁን እንጅ ዳግም ወረራ ተፈጽሞበት በደኅንነት ስጋት ውስጥ ይገኛል ብለዋል፡፡
መንግሥት የራያን ሕዝብ ፍላጎት ያውቃል፤ ሕወሓትም የራያ ሕዝብ እንደማይፈልገው ጠንቅቆ ያውቃል፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይሄን ተረድቶ ለራያ ሕዝብ ፍትሕ እንዲሰጠው ከጎኑ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡
የራያ ሕዝብ ማንኛውንም ችግር ደም አፋሳሽ ባልኾነ መንገድ፤ ወንድማማችነትን እና ዘላቂ አብሮነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ችግሮቹ እንዲፈቱ ፍላጎቱ ነው፤ ተፈናቃይ የሚባሉ ሰዎች ተመልሰው ሕይወታቸውን እየመሩ ነው የነበረው፣ አሁን ግን ተረጋግቶ ሲኖር የነበረውን፣ ሰፊውን እና እውነተኛውን የአካባቢው ማኀበረሰብ አፈናቅለው አዲስ ሰው እያመጡ ነው፣ እውነተኛውን አፈናቅሎ የሚመጣ ሰላም የለም ብለዋል፡፡
በሕገወጥ መንገድ ወደ አካባቢው የገቡ ታጣቂዎች ተመልሰው ሕጋዊ የኾነው ማኅበረሰብ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲኖር መንግሥት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች እየቀረበላቸው ያለውን የሰላም ጥሪ እያከበሩ አይደለም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የታጠቀ ኀይል እያሰፉ፣ አካባቢውንም እየወረሩ ነው ብለዋል፡፡ በሚሊዮን የሚገመቱ የማይታወቁ የትግራይ ነዋሪዎችን ሐሰተኛ መታወቂያዎችን እየሰጡ እያስገቡ ነው፤ ወደ ራያ እየገቡ ያሉት ራያን አይተውት የማያውቁ አዲስ ሰፋሪዎች ናቸው ይላሉ፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳደሪ እና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ታምራት ንጋቱ በዞኑ ሥር በሚተዳደሩ ሦስት የራያ ወረዳዎች ላይ ሕወሓት ወረራ ፈጽሞባቸዋል ብለዋል፡፡ በወረራው ምክንያት ቁጥራቸው በርከት ያሉ የኅብረሰተብ ክፍሎች ተፈናቅለዋል፤ በአካባቢው ይሰጡ የነበሩ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ አገልግሎቶች በሙሉ ተቋርጠዋል፤ ማኅበረሰቡም ለዳግም እንግልት እና ስቃይ ተጋልጧል ነው ያሉት፡፡
የተፈጸመው ወረራ ከሕግና ከሥርዓት ውጭ በመኾኑ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በመንግሥት ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል፤ ነገር ግን የትግራይ ወራሪ ኀይሎች አካባቢውን ተቆጣጥረው በመያዝ በማኅበረሰቡ ላይ ሰፊ እንግልት እየፈጸሙ ነው፤ ይባስ ብሎ ወረራውን እያሰፉ ነው ብለዋል፡፡
የራያ ሕዝብ ለዓመታት ማንነታችን አማራ ነው በማለት ጽኑ አቋም ይዞ ሲታገል ኖሯል፤ ማንነት በምንም መልኩ ሊቀየር አይችልም፣ የትኛውም አይነት ፖለቲካ ቢሠራ እውነተኛውን ማንነት መቀየር እንደማይቻል ሲያሳይ ኖሯል ነው ያሉት፡፡
የሕወሓት ወራሪ የራያን እውነታ በኀይል ልደፍጥጥ በሚል ነው ወረራ የፈጸመው ብለዋል፡፡ ከጦርነት ያገኘነው ጥቅም የለም፤ ማንነትን በጉልበት መደፍጠጥ አይቻልም፤ ማንነትን መደፍጠጥ እንደማይቻል የአካባቢው ማኅበረሰብም የመንግሥት አቋምም ነው ይላሉ፡፡ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሲቻል አሁንም በኀይል አሥተዳድራለሁ የሚል ግትር አቋም ያለው ኀይል በሕዝባችን ላይ እየፈጸመው ያለው ድርጊት አሰቃቂ ነው፤ ችግሩን ለመቀልበስ ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
የራያ ሕዝብ ጉዳዩ በሰላም ማለቅ አለበት የሚል ጽኑ አቋም ስላለው ያን እየጠበቀ ነው፤ ነገር ግን ይሄን እንደፍርሃት የቆጠረው ወራሪ ኀይል በሕዝብ ላይ በደል እየፈጸመ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የራያ ሕዝብ ለዓመታት ባደረገው ተጋድሎ እና መስዋዕትነት ነጻ ወጥቷል ያሉት ምክትል አሥተዳደሪው ባለፉት ዓመታትም በነጻነት ራሱን በራሱ ሲያሥተዳድር ቆይቷል፤ አሁን ግን በነጻነት ራሱን በራሱ የማሥተዳደር መብቱን እንዳያስቀጥል ወራሪ ኀይሎች መሰናክል ኾነውበታል ብለዋል፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ ለባርነት፣ ለጭቆና እና ለእንግልት የሚዳርገውን የትኛውንም ኀይል አንቀብልም፤ መንግሥት ሊደርስልን ይገባል እያለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
መንግሥት ለተፋናቃይ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ነገር ግን እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አይደለም ነው ያሉት፡፡
መንግሥት ዘላቂ በኾነ መንገድ የአካባቢውን ጥያቄ ለመመለስ፤ ሕዝብንም ከእንግልት ለመታደግ እየሠራ ነው፡፡ የራያ አማራ ማንነትን በኀይል መውሰድ አይቻልም፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ለማንነቱ ዋጋ እየከፈለ ያለውን ማኅበረሰብ ሊደግፈው ይገባዋል ብለዋል፡፡
ከትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር በተደጋጋሚ የሚሰጡት መግለጫዎች እና ራያን በተመለከተ የሚሰጡ ሃሳቦች ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው፤ የትግራይ ሕዝብ እንዲህ አይነቱን ጸብ አጫሪ አካሄድ በቃ ሊል ይገባዋል ነው ያሉት፡፡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደሩም ቆም ብሎ ሊያስብበት እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡