የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በልብና በካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
የኮሌጁ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር አንዱዓለም ደነቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በልብና በካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ሆስፒታሉ የልብና የካንሰር የልህቀት ማዕከል ለመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ በቀጣይ ዓመት መስከረም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ በሚዘረጋው መዋቅር የልህቀት ማዕከላቱ ተቋማዊ ቅርጽ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ሆስፒታሉ የልብ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም በልብ ሕክምና ሰፊ ምርምር በማድረግና ባለሙያዎች በተወሰኑ ዘርፎች እንዲሰለጥኑ (ስፔሻላይዜሽን) በማድረግ ሆስፒታሉን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
የሕክምና ማዕከሉን አገልግሎት ሊያጠናክሩ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች መገጠማቸውንም ፕሮፌሰር አንዷለም ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ሆስፒታሉን የካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የሕክምና ግብዓት በማሟላት፣ የዘርፉን የሰው ኃይል በማሰልጠንና ሌሎች አስፈላጊ ሥራዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲከናወኑ መቆየቱን ተናግረዋል።
ለዚህም ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ የልህቀት ማዕከል ሲሆን ከመደበኛው ሥራ በተጨማሪ ለልብና ለካንሰር ታካሚዎች ከምርመራ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዘልቅ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችልና በሁለቱ ዘርፎች ተጠቃሽ የምርምር ማዕከል ያደርገዋል ብለዋል።
(ኢዜአ)