አንድ የወንጀል ቅጣት በተለያዩ ሁኔታዎች (በምሕረት ወይም ይቅርታ) የተነሳ ቀሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የሰዎች የቀደመ የወንጀል ታሪክ በቀጣይ ህይወታቸው ወይም ኑሯቸው ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በመሆኑም ቀድሞ በወንጀል ተቀጥቶ ቅጣቱን የጨረሰ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚፋቅለት በወንጀል ሕጉ እና በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ በተቀመጡት ድንጋጌዎች መሰረት አቤቱታውን አቅርቦ የወንጀል ቅጣቱን ጥሎበት በነበረው ፍርድ ቤት ሲሰየም ነው፡፡ መሰየም በወንጀል ሕጋችን የተካተተ ፅንሰ ሀሳብ ቢሆንም ቃሉ፣ በሕጉ ያለው ትርጓሜም ሆነ ዝርዝር ሁኔታው በማህበረሰባችን እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ በዚህ የግንዛቤ ክፍትት ምክንያት በስፋት ሲጠቀምበት አይስተዋልም፡፡ ስለሆነም በዚህ አጭር ጽሁፍ ለማህበረሰቡ መሰየምን አስመልክቶ ግንዛቤ ማስጨበጥን ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን የመሰየም ምንነት፣ ውጤቱን እና የሚፈፀምበትን ዝርዝር ሁኔታ እንዲሁም የመሰየም ውሳኔ መሻር የምንመለከት ይሆናል፡፡
የመሰየም ምንነት
መሰየም የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ስም መስጠት ወይም ስም ማውጣት መሆኑን በተለያዩ መዝገበ ቃላት እናገኘዋለን፡፡ ይህ ግን ሕጉ ማለት የፈለገውን በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል ላይሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ የወንጀል ሕጉ በእንግሊዝኛ ቅጂው የተጠቀመው “Reinstatement” የሚለው ቃል የተሻለ አመላካች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት (Black’s law dictionary) በ8ኛ እትም “Reinstatement” የሚለውን ቃል “To place again in a former state, condition, or office; to restore to a state or position from which the object or person had been removed.” በሚል ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡ ይህን ትርጓሜ ወደ አማርኛ ስንመልሰው በአጭሩ አንድን ነገር ወይም ሰው ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ መመለስ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ህጉ በዚህ ክፍል የሚገልፀው ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ስለመመለስ መሆኑን ጠቋሚ ነው፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 232(1) መሰየም የተወሰነበትን ቅጣት የፈፀመ ወይም ቅጣቱ በይርጋ ወይም በይቅርታ የቀረለት ወይም ፍርዱ ወይም የቅጣቱ አፈፃፀም ያታገደለት ወይም በአመክሮ የተለቀቀ ማንኛውም ጥፋተኛ በሕጉ የተቀመጡትን ግዴታዎች በመፈፀም ከመቀጣቱ በፊት የነበረውን ንፁህ ስም እንዲመለስለትና ፍርድ እንዲሰረዝለት የሚጠይቅበት ሂደት ስለመሆኑ ይገልፃል፡፡ መሰየም የሚገኘው በመልካም ሥራ ነው ፡፡ እንደ መብት በይገባኛል የሚጠየቅ አይደለም፡፡ መሰየም በቀድሞው ጥፋተኛ (ፍርደኛ) በግሉ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ በሕጋዊ ወኪሉ ወይም በቅርብ ዘመዱ ጠያቂነት የሚቀርብና በፍ/ቤት መወሰን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ለመሰየም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች
መሰየም በዘፈቀደ የሚከናወን ሳይሆን ቅድመ ሁኔታዎች ያሉት ስለመሆኑ በአንቀጽ 233 ተደንግጓል፡፡ አንድ ፍርደኛ መሰየም የሚችለው፡-
ሀ. የተወሰነበትን ቅጣት የፈጸመ ወይም ቅጣቱ በይርጋ ወይም በይቅርታ የቀረለት ወይም ፍርዱ ወይም የቅጣቱ አፈፃፀም የታገደለት ወይም በአመክሮ የተለቀቀ ሰው ሊሆን ይገባል፣
ለ. የተወሰነበት ቅጣት ፅኑ እስራት፣ እስከመጨረሻው ከሀገር መውጣት ወይም የንብረት መወረስ ከሆነ ቅጣቱ ከተፈፀመ ወይም በይርጋ ከታገደበት ቀን አንስቶ፣ ቅጣቱ በይቅርታ ምክንያት ተሽሮ ከሆነ ተቀጪው ከተለቀቀበት ቀን ጀምሮ፣ ተቀጪው ቅጣቱ ታግዶለት ወይም በአመክሮ ተፈትቶ የፈተናውን ጊዜ በሰላም ጨርሶ ከሆነ ቅጣቱ ከታገደበት ወይም በአመክሮ ከተፈታ ቀን ጀምሮ ቢያንስ አምስት ዓመት ያለፈ እንደሆነ በሌላው ሁኔታ ግን ቢያንስ ሁለት አመት የሆነ መሆን፣
ሐ. በተጠቀሰው የአምስት ወይም የሁለት አመት ጊዜ ውስጥ በመልካም ጠባይ የተመራ መሆንና በማናቸውም በእስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ አለመገኘት፣
መ. የተወሰነበት ተጨማሪ ቅጣት ካለ ይህ ቅጣት ፈፅሞ መገኘት፣
ሠ. የተለቀቀው ተቀጪ የራሱ ችሎታና የጊዜው ሁኔታ በሚፈቅድለት መጠንና እራሱ ሊፈፅመው ይገባዋል ተብሎ በሚገመትበት ሁኔታ በፍርድ የተወሰነበትን ካሳ፣ የዳኝነት ማንኛውንም አይነት ኪሳራ በሚገባ አጠናቆ ከፍሎ መገኛት ይጠበቅበታል፡፡
በፊደል (ሀ) ላይ ከተመለከተው ጊዜ ጋር በተያዘ ቅጣቱ የታገደው በይርጋ ከሆነ ግለሰቡ ቅጣቱን ፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ቅጣቱ ያበቃ ከነበረበት ጊዜ ከማለፉ በፊት ሊሰየም እንደማይችል ከአንቀፅ 234 (1) ንባብ መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በአንቀፅ 224(1)(ለ) ሥር ከአስር ዓመት በላይ ለሆነ የነፃነት የሚያሳጣ ቅጣት የይርጋ ጊዜ ሀያ አመት ነው፡፡ አንድ ጥፋተኛ የተባለ ሰው የተፈረደበት ሀያ አምስት አመት ቢሆን የይርጋ ጊዜው በአንቀፅ 225 መሰረት ፍርዱ የመጨረሻ ሆኖ ተፈፃሚ መሆን ከሚችልበት ቀን ጀምሮ የሚቆጠር በመሆኑ ቅጣቱ ተፈፅሞ ቢሆን ኖሮ ከይርጋ በፊት አይጠናቀቅም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅጣቱ በይርጋ የሚታገድ ቢሆን እንኳን ቅጣት ቢፈፀም ሊጠናቀቅ ከሚችልበት ቀን በፊት ፍርደኛው ሊሰየም አይችልም፡፡
በተጨማሪ መሰየም ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ላይ በሚወሰኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በወንጀል ህጉ አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ የሚባለው ዘጠኝ እና በአስራ አምስት አመት መካከል ያለ ልጅን የሚወክል ነው፡፡ በዚህ እድሜ ክልል የሚገኙ ልጆች ለአካለመጠን ያልደረሱ በመሆናቸው የሚወሰንባቸው የእርምት እርምጃ በአዋቂ አጥፊዎች ላይ ከሚወሰነው ቅጣት የሚለይ ስለመሆኑ አንቀፅ 157 እና ተከታዮቹ ተመልክተዋ ይገኛሉ፡፡
አካለመጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የሚወሰኑ የእርምት እርምጃዎች ወደ ህክምና ተቋም መላክ፣ ቁጥጥር በማድረግ ትምህርት እንዲሰጠው ማድረግ፣ ተግሳፅና ወቀሳ፣ በትምህርት ቤት ወይም በመኖሪያ ቤት ተወስኖ እንዲቆይ ማድረግ፣ ወደ ጠባይ ማረሚያ ተቋም መላክ፣ አለፍ ሲልም ወንጀሉ ከባድ ሲሆን እስራትም የሚጨምር ነው፡፡ ከእስራት ቅጣቱ በስተቀር የሚወሰኑ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ሌሎች ቅጣቶች ቅጣት በተፈፀመ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለማሰየም የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሲሟሉ ሊሰየም እንደሚችል በአንቀፅ 175 ሥር ተደንግጓል፡፡ አካለመጠን ያልደረሰው ልጅ የሚሰየመው እራሱ ወይም በእርሱ ላይ በሕግ ስልጣን ያላቸው ሰዎች ሲጠይቁ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ስሙ እንዲታደስለት የሚጠይቀው ተቀጪ በህዝባዊ፣ በወታደራዊ ወይም በማህበራዊ አገልግሎት መስክ የሚያስመሰግን ልዩ አስተዋፅኦ ያበረከተ እንደሆነ ለመሰየም የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት መሰየም ሊፈቀድት እንደሚችል በአንቀፅ 234 (2) ተደንግጓል፡፡ ይህ የተለየ ማህራዊ፣ ህዝባዊ ወይም ወታራዊ አበርክቶ በሕጉ የተብራራ ባለመሆኑ እንደየ ሁኔታው በፍርድ ቤት የሚመዘን ይሆናል ማለት ነው፡፡
ፍርደኛው ለመሰየም የሚያቀርበው ጥያቄ ከላይ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ያላሟላ ከሆን ወይም ፍርድ ቤቱ ለመሰየም የቀረበው ጥያቄ በቂ አይደለም ብሎ ካመነ የመሰየም ጥያቄውን አለመቀበል ይችላል፡፡ ይህ በሆነ ጊዜም መሰየም የጠየቀው ፍርደኛ በድጋሚ መሰየም ጥያቄ ማቅረብ የሚችል ቢሆንም ሁለት አመት እሲኪያልፍ መጠበቅ አለበት (አንቀጽ 236) ፡፡
የመሰየም ውጤት
አንድ ተቀጪ የመሰየም ጥያቄ አቅርቦ ጥያቄውን ፍርድ ቤቱ ከተቀበለው እና ከሰየመው መሰየሙ የሚያስከትላቸው ውጤቶች በወንጀል ህግ አንቀጽ 235 ንዑስ አንቀጽ ከ1-3 ተመልክተዋል፡፡ እነርሱም፡-
ተቀጪው ከተሰየመበት ጊዜ ጀምሮ ተወስኖበት ከነበረው ከመብት፣ ከማዕረግ ወይም የችሎታ ማጣቱ ቀርቶለት ህዝባዊ መብቱንና ቤተሰብ ማስተዳደርና የሙያ ሥራ የመሥራት መብቱን እንደገና ለመያዝ ችሎታ ይኖረዋል፣
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ሙያዊ ሥራውን የመስራት መብቱን እንደገና ለመያዝ ችሎታ ያገኛል ሲባል ፍርደኛው ተቀጥሮ የሚሰራ ከሆነ የቀድሞ ቀጣሪው ጋር እንደመብት ይመለሳል ማለት ሳይሆን የተወሰነበት ፍርድ በሙያው የመስራትን መብት ነፍጎት ከሆነ ቀድሞ በነበረው ሙያ የመስራት መብት ያገኛል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ከወንጀል ጥፋኝነት ነፃ መሆን የሚጠይቅ እንደመሆኑ የወንጀል ሪከርዱ እስካለ ድረስ ፈቃዱን ሊያገኝ አይችልም፡፡ ከተሰየመ ግን ይህ የቀድሞ ጥፋኝት ሪከርድ ቀሪ ስለሚሆን የጥብቅና ፈቃዱን የማግኘት መብት ይሰጠዋል፡፡
የቅጣቱ ፍርድ ከወንጀለኞች መዝገብ ላይ ይፋቅለታል፣ ለወደፊትም እንዳልተፈረደበት ይቆጠራል፣
በመሰየም የተሠረዘውን ቅጣት አንስቶ ተቀጪውን መውቀስ ወቃሹን በስም ማጥፋት ወንጀል ያስቀጣል፣ ለሕዝብ ጥቅም የተደረገ ነው ብሎ መከላከልም አይቻልም፡፡ ይህ ማለት ፍርደኛው ሌላ ወንጀል ፈፅሞ ቢገኝ እንኳን ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡ አስቀድሞ የተሰየመበትን ፍርድ በሪከርድነት ሊያቀርብበት አይችልም ማለት ነው፡፡
የመሰየም ውሳኔ መሻር
አንድ ፍርደኛ ከተሰየመ በኋላ በኋላ የሚያሳየው ባህሪ መሰየሙ እንዲሰረዝበት የሚያደርግ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኸውም እንዲሰየም ከተፈቀደለት በኋላ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ በሞት ወይም በፅኑ እስራት እንዲቀጣ የመጨረሻ ፍርድ ከተሰጠበት አስቀድሞ እንዲሰየም የተሰጠው ውሳኔ ይሰረዛል፣ በድጋሚም እንዲሰየም አይፈቀድለትም (አንቀጽ 237)፡፡ ፅኑ እስራት የሚወሰነው ከባድ ወንጀል ባደረጉ እና ለህብረተሰቡ አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ ሲሆን ይህም ከአንድ ዓመት እስከ ሀያ አምስት ዓመት የሚደርስ እንደሆነ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 108 ላይ ተደንጎ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ መሰየም በሕጉ የተሰጠው ትርጓሜ እና ለመሰየም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ከላይ የተመለከቱት ሲሆኑ በወንጀል ጥፋኝነት የተወሰነባቸው እና ከላይ በሕጉ መሰረት ለማሰየም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟሉ ፍርደኞች በማሰየም የቀድሞ ጥፋተኝነት ሪከርድ በማሰረዝ መልካም ስማቸውን እንዲላበሱ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡
Via ministry of justice በንቃተ ህግ፤ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት