በከፍተኛ የፋይናንስ ብክነትና ህግ ያልተከተለ አሰራር ለከፍተኛ የሃብት ዘረፋ መጋለጣቸው በተደጋጋሚ የሚነሳባቸውን የሃይማኖት ተቋማት የፋይናንስ አሰራር ደንብ እንዲሁም የኦዲት ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ። ሪፖርቱ እንደ አስፈላጊነቱ ለህዝብ በአመቺ መንገድ ይገለጻል። ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በስፋት ውይይትና ምክክር የሚደረግበት መሆኑም ተሰምቷል።
“የሃይማኖት ጉዳዮች አዋጅ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ረቂቅ ህግ በግርድፍ ያወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳለው ረቂቁ ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርቱን ለሰላም ሚኒስቴር ማቅረብ እንደሚኖርበት፣ ከውጭ አገር የሚመጣ የገንዘብ ዕርዳታ በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት ይደነግጋል።
የሃይማኖት ተቋማቱ ተቀባይነት ያለው የሒሳብ አያያዝና የኦዲት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚኖርባቸው፣ የኦዲት ሪፖርታቸውንም ለሰላም ሚኒስቴር ማቀረብ እንዳለባቸው በረቂቅ አዋጁ ተካቷል።
የሃይማኖት ተቋማቱ የሚጠቀሙት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት የገቢ፣ የወጪና አጠቃላይ የንብረት ዝርዝር የያዘ መሆን እንደሚኖርበትና የገቢ አሰባሰብና የወጪ አስተዳደር በሕጋዊ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡ አንድ የሃይማኖት ተቋም በራሱ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በሚያከናውንበት ጊዜ፣ ለዚሁ ሥራ የተለየ የባንክ ሒሳብ መክፈትና የተለየ መዝገብ መያዝ እንዳለበት ደንግጓል፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ከውጭ አገር የሚላክለትን የገንዘብ ዕርዳታ፣ ስጦታ ወይም ሌሎች የገንዘብ ድጋፎችን በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማሳወቅ እንደሚኖርበት አስቀምጧል፡፡ ሲያሳውቅም የለጋሹን ድርጅት ወይም ግለሰብ ስምና አድራሻ፣ የተለገሰው የገንዘብ፣ ስጦታ ዓይነትና መጠን፣ እንዲሁም ስጦታው ወይም ድጋፉ የተሰጠበት ልዩ ዓላማ መካተት እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሦስት ወራት ውስጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በገለልተኛ ኦዲተር ማስመርመር እንዳለበትና የኦዲተሩን አቋምና የውሳኔ ሐሳብ መያዝ እንዳለበት በረቂቁ ተመላክቷል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የደረሰውን የኦዲት ሪፖርት አመቺ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንዳለበትም ተደንግጓል፡፡
የአምልኮ ወይም የመቃብር ቦታ አሰጣጥን በተመለከተም ለሃይማኖት ተቋማቱ የመሬት አቅርቦት በመሬት አጠቃቀምና የሊዝ ሕጎች መሠረት እንደሚወሰን ተገልጿል፡፡ ለአምልኮ ወይም ለመቃብር ቦታ በተጠየቀበት አካባቢ ለሃይማኖት ተቋሙ ለተመሳሳይ ዓላማ የተሰጠ ቦታ አለመኖሩ ወይም ተጨማሪ ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት፣ እንዲሁም በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል የሚኖረው ርቀት ቢያንስ 500 ሜትር መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
ትምህርትና የሃይማኖት ተግባራትን በሚመለከትም በረቂቁ ላይ ዝርዝር ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ መደበኛ ትምህርት በሚሰጡ የመንግሥት ወይም የግል ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ሃይማኖታዊ ይዘት የሌለው መሆን እንደሚኖርበት ተመልክቷል፤ በእነዚሁ የመንግስትና የሃይማኖት ተቋማት ንብረት ባልሆኑ የግል የትምህርት ተቋም ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃይማኖታዊ ትምህርትን ማስተማር ወይም በቡድን ማምለክ የተከለከለ ነው የሚል አሳብም አለበት።
በተጨማሪም ማንነትን ለመለየት የሚያስችሉ ሃይማኖታዊ አለባበሶችን ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደማይገባ ተደንግጓል፡፡ ይህን የረቂቁን ክፍል አስመልክቶ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደ ቤተ እምነቱ አስገዳጅ ሕግጋቶች ልዩ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ መደንገግ ሲገባው፣ ሙሉ ለሙሉ ከትምህርትና ሥራ ገበታ የሚያስገድዱ ድንጋጌዎችን መያዙ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ለሰላም ሚኒስቴር በላከው አስተያየት፣ ቅሬታና የመፍትሔ ሐሳብ መግለጹ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የመንግሥት ኃላፊዎች መንግሥትን ወክለው በሃይማኖት በዓላት አከባበር ላይ መገኘት እንደማይችሉ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በትምህርት ቤት፣ በመኖሪያ ቤትና በሕክምና ማዕከላት አካባቢ የሚደረግ አምልኮ በአካባቢ ጥበቃ ሕግ የተቀመጠውን የድምፅ መጠን ያከበረ መሆን እንደሚኖርበት፣ ካልተፈቀደ በስተቀር ማስተማርን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ተግባራትን በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች መፈጸም እንደማይችል ረቂቁ ይደነግጋል፡፡
የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በበኩሉ ይህ የረቂቅ አዋጁ ክፍል በልዩ ሁኔታ በወንጌል አማኞች ላይ ጫና የሚፈጥርና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው መሆኑን በመግለጽ፣ ሊስተካከል ይገባል በማለት ለሚኒስቴሩ በላከው ደብዳቤ ማስታወቁን ሪፖርተር አስታውሷል።
ዜናው በሃይማኖት ተቋማት ዙሪያ ጫጫታ መፍጠሩ እያተሰማ ነው። በአብዛኛው የእምነት ተቋማት የሚሰማው ግጭትና አለመግባባት የዚሁ የሃብት ቅርምት ጉዳይ እንደሆነ ከራሳቸው መሰማቱ አይዘነጋም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ይህን ሲሰሙ በነበረበት ውይይት ላይ ህግ እንደሚዘጋጅና የሚመለከታቸው መክረውበት እንደሚጸድቅ መናገራቸው አይዘነጋም።
ኢህአዴግ በግምት ከዛሬ አስራ አምስት በፊት አገልጋዮች ላይ ያተኮረ የሃብት ምርመራ አካሂዶ በሚታወቁ ፓስተሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አስተዳዳሪዎችና ወዘተ ስም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዳከማቹ አረጋግጦ ነበር። በሃይማኖት ተቋማት የሚካሄደው ህግን ያልጠከተለ የፋይናንስ አካሄድ ለዝረፋ አመቺ በመሆኑ አዋጁ ከፍተኛ ተግዳሮት ሊገጥመው አንደሚችል ይገመታል።
አስተያየት የሚሰጡ እንደሚሉት እነዚህ አካላት ሃብት ስላላቸው የአዋጁን አቅጣጫና አላማ በማጣመም ምዕመኑን ለማነሳሳት ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ፣ በግርድፍ የሚወጡ መረጃዎችን ፍትህ ሚኒስቴር በሚቻለው የሚዲያ አውድ ሁሉ ለህዝብ በመደጋገም ሊያሳውቅ ይገባል ብለዋል። አያይዘውም ከሃይምኖት ተቋማቱ ጋር የሚደረገው ውይይት ህዝብ እንዲሰማው ክፍት ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።