” ከፍጹም ሀሰተኛ መረጃ ተጠንቀቁ ” የጠ/ሚ ጽ/ቤት
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገውን የመግባቢያ ስምምነት (MoU) እንደሰረዘው ተደረጎ የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው።

የጠ/ሚ ጽ/ቤት ያወጣው መግለጫ አስመስሎ አንድ የተቀነባበረ የጠ/ሚ ጽ/ቤት አርማ ያለበት መግለጫ በስፋት እየተዘዋወረ ይገኛል።
ይኸው መግለጫ ፦
- ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ከተለየችው ‘ ክልል ‘ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት (MoU) እንደሰረዘችው ፤
- ኢትዮጵያ ከዩኬ፣ ከG7 እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወያይታ የሶማሌላንድን ሉዓላዊ ሀገርነት የምትደግፍበት ማስረጃ እንዳላገኘች
- የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሁን በኃላ ህጋዊ ያልሆነ ስምምነት ከሶማሌላንድ ጋር እንደማያደርግ
- ኢትዮጵያ ፤ የሶማሌላንድ ጉዳይ የሶማሊያ ስለሆነ ፖለቲካዊ ችግራቸውን በአንድ ሀገር ጥላ ስር እንዲፈቱ እንደምትተው … የሚገልጽ ነው።
ይህ ግን ፍጹም ሀሰተኛና መግለጫው የተቀነባበረ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ምን አለ ?
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፤ ከሶማሌላንድ ጋር ስለተፈጸመው የመግባቢያ ስምምነት በኦንላይን እየተዘዋወረ እና እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍጹም ሀሰተኛ / የውሸት ይዘት ስለሆነ ህዝቡ እንዲጠነቀቅ መክሯል።
በሀገር ውስጥ ፣ በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች መግለጫም ሆነ መረጃ የሚሰጠው በይፋዊ የጽ/ቤቱ ገጾች / ቻናሎች ላይ ብቻ እንደሆነ አመልክቷል።
ሁሉም ሰው የጽ/ቤቱን ይፋዊ አርማ በመጠቀም ከሚሰራጩ እንደዚህ አይነት የውሸት መረጀዎች / ይዘቶች እራሱን እንዲጠብቅ አደራ ብሏል።