ዘጠኝ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የዋጋ ግምት ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በመስረቅ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ግብራበሮቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ከተሰረቁት ተሽከርካሪዎች መካከል አንደኛው ለመንገድ ኮሪደር ልማት ስራ የገባ መሆኑ ተውቋል፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ እየተከናወነ ለሚገኘው የመንገድ ኮሪደር ልማት ስራ ወደ ሃገር ውስጥ የገባውና ንብረትነቱ ሲ.ሲ.ኢ.ሲ.ሲ የተባለ የቻይና ድርጅት የሆነው ከባድ የጭነት ተሽከርካሪ ሰሌዳ ያልተለጠፈለት አዲስ መኪና ነው፡፡
አምስት ሚሊዮን ብር የዋጋ ግምት አለው በተባለው በዚህ ተሽከርካሪ ላይ የስርቆት ወንጀል የተፈፀመው መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 9 ፡30 ሰዓት ገደማ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ድንበሯ ሆስፒታል አካባቢ እንደሆነ በአዲስ አበባ ፖሊስ የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ሽፈራው ጉቱ ገልፀዋል።
በቀጥታ በወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ተሽከርካሪው ወደ ቆመበት ስፍራ ሄደው የጥበቃ ሰራተኞቹን ካግባቡ በኋላ ተመሳጥረው መኪናውን ሰርቀው እንደተሰወሩ ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
ፖሊስ የወንጀሉ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ የምርመራ እና የክትትል ቡድን በማቋቋም የተሰረቀውን ተሽከርካሪ ለማስመለስ እና ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
እንደ ረዳት ኮሚሽነር ሽፈራው ጉቱ ገለፃ ተሽከርካሪው ታይቷል በተባለባቸው ከአዲስ አበባ ውጪ ወደሚገኙ የክልል ከተሞች ጭምር በመሄድ መረጃ የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል ። አዳማ፣ መተሃራ ፣ ጅግጅጋ እና ሃረር የክትትል ስራው ከተከናወነባቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ የክትትል እና የምርመራ ቡድን አባላት ሃረር ከተማ ላይ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በተደረገ ምርመራ ተሽከርካሪው ተሽጦ አፋር ክልል ውስጥ እንደሚገኝ ማረጋገጥ እንደተቻለ ረዳት ኮሚሽነር ሽፈራው ጉቱ አስረድተዋል።
የተሰረቀው ተሽከርካሪ ሀሰተኛ ቦሎ እና ሀሰተኛ የ3ኛ ወገን የመድን ሽፋን እንዲሁም ኮድ 3- A20078 ኢት የሆነ ሰሌዳ ለጥፎ ሲንቀሳቀስ በምርመራና ክትትል ቡድኑ አባላት በአፋር ክልል በርሀሌ በተባለ አካባቢ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡
ፖሊስ ባከናወነው ተጨማሪ ምርመራ ንብረትነቱ የወይዘሮ ሂሩት ብርሀኑ የሆነ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- 86484 አ.አ ፒካፕ ደብል ጋቢና ተሽከርካሪ በእነዚሁ ተጠርጣሪዎች መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ካርል አደባባይ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ እንደተሰረቀ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
4.5 ሚሊዮን ብር የዋጋ ግምት አለው የተባለው ይህ ተሽከርካሪ ባለንብረቷ ከቀጠሩት የጥበቃ ሰራተኛ ጋር በመመሳጠር እንደተሰረቀ የጠቀሱት ረዳት ኮሚሽነሩ፤ የራሱን ሰሌዳ በመቀየር ከሌላ ተሽከርካሪ ላይ የተሰረቀ ኮድ 2-C25939 አ.አ የሆነ ሰሌዳ ለጥፎ በግለሰብ ግቢ ውስጥ ቆሞ መገኝቱን አብራርተዋል። በአጠቃላይ 10 ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ባደረገው ጥረት ተይዘው ምርመራ እየተጣራ ሲሆን የተሰረቁት ሁለት ተሽከርካሪዎችም ተመልሰዋል፡፡
ስነ ምግባር የጎደላቸው አንዳንድ የጥበቃ ሰራተኞች ከወንጀል ፈፃሚዎች ጋር በመተባበር የግለሰቦች እና የተቋማት ንብረቶች እንዲዘረፉ እያደረጉ የሚገኙ መሆናቸውን ያስታወሱት ረዳት ኮሚሽነር ሽፈራው፤ አሰሪዎች የተለያዩ ዘዴዎችን ተቅመው ለክትትል እና ቁጥጥር ስራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡
ከአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ግንኙነት ያላቸው የክልልም ሆነ የከተማ ትራንስፖርት መ/ቤቶች ከተለያዩ ቦታዎች ለተሰረቁ ተሽከርካሪዎች ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ሰሌዳ እና ሊብሬ ለማውጣት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተገንዝበው ተገቢውን የማጣራት ስራ እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም
Via police fb page