የመንግስት ደጋፊዎችና አብረውት የሚሰሩት አንድ አንቀጽ ሳያነቡ በደፈና “የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ሰነድ ተጋለጠ” በሚል ያሰራጩት አድራሻ እንጂ ባለቤት የሌለው የህቡዕ ሪፖርት “ሸኔ ተመቷል” ይላል። መልሶ ደግሞ ኦነግ ሸኔ የትግል ስትራቴጂውን እንደቀየረ ያመልክታል።
ኦነግ ሸኔ የቀየረውም ስትራቴጂ መተሪያ ስያሜ “ኦፕሬሽን ኢርቡ ሺኒጋ” ይሰኛል። ትርጉሙም “የሰማዕታት ቃል ኪዳን ማለት ነው” እነማን እንዳዘጋጁት ፍንጭ የማይሰጠው ሪፖርቱ፣ ኦነግ ሸኔ የተባለውን አዲስ የትግል ስልት የመረጠው ያታውን ተቀባይነት መልሶ ለማግኘት በማቀድ እንደሆነ ያትታል።
ከወር በፊት ጃል መሮ “ወለጋ በቃን” በማለት መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል። “የተቀባ” የሚል መለኮታዊ ስም የተሰጠው የኦነግ ጦር በአምስት አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያመራም ጃልመሮ መናገራቸውን አብረን ጠቅሰን ዘግበን ነበር። ጃልመሮ በዙም ስብሰባ ለውስን አስተባባሪዎች እንዳሉት ኦነግ በወለጋና አካባቢው ስልተና ላይ ካሉ ወታደሮች በቀር ሃይሉን አስወጥቷል።
ይህ የህቡዕ ሪፖርት እንዳለው አዲሱ የኦነግ ሸኔ ስልት ተብሎ የቀረበው የቀጥታ ጦርነት ግጥሚያ ማቆም ነው። አድፍጦ የማጥቃት ስልትን ዋንኛው ዘዴው አድርጓል። በዚሁ መሰረት ኦነግ አሁን ላይ ራሱን ያዘጋጀው የመንግስት ሃብትን መዝረፍ፣ ትጥቅ የሚከማችባቸውን መጋዘኖች ማጥቃት፣ የመንግስት ባለስልጣናትን ማደን፣ በጥቅሉ መንግስትን ያዳክማል ተብሎ በሚታመንባቸው አግባቦች ሁሉ በህቡዕ ወይም በደፈጣ አደጋ ማድረስ ነው።
ላለፉት አራትና አምስት ተከታታይ ዓመታት መከራውን ያየው የወለጋና አካባቢው ህዝብ “በቃ” በሚል ከመንግስት ጋር በመቆሙ የተነሳ ከመንግስት የጸጥታ አካላትና ከክልሉ አመራሮች ጋር አብሮ በመቆሙ ኦነግ ሸኔ ክፉኛ እንደተጎዳ ምስክሮች ይናገራሉ። የመንግስት ሃይሎች ኦነግ ሸኔ በታሪኩ ተወስዶበት የማያውቀውን መቀመጫውን ሳይቀር ተነጥቋል። የመንግስት የጸጥታ መዋቅር አመራሮችና የክልሉ ሃላፊዎች በተደጋጋሚ እንዳሉት ኦነግ ሸኔ እንደ ድርጅት ወደ መክሰም እያመራ ነው።
ሪፖርቱ ኦነግ ሸኔ መመታቱን ጠቅሶ እዛው መልሶ የትግል ስትራቴጂ ለውጥ በማድረግ መለኮታዊ ስም ለራሱ በአዲስ ሰይሞ መነሳቱን ያስረዳበት አጋባብ አልተካተተም።
ራሱን “ነብይ” የሚል ስም ያጎናጸፈውና ማን እንዳዘጋጀው በይፋ የማይገልጸው ሪፖርት ይፋዊ መጠሪያው vatescorp.com የሚል ሲሆን፣ vates ማለት በላቲን prophet ወይም Fortune teller የሚል ትርጉም አለው። ይህንኑ ስያሜውንና ትርጉሙን ያተመው ክፍል ናይሮቢ ቢሮ እንዳለው ከመግለጹ ውጪ ባለቤቱ፣ ተባባሪ ዘጋብዎቹም ሆኑ በገንዘብ የሚደግፈው አካል ማን እንደሆነ ምንም የተገለጸ ነገር የለም።
ይህንኑ ተከትሎ አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጠው አብረዋቸው የሚሰሩ ስለመኖራቸው ፍንጭ እየሰጡ ነው። ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታተሙና የሚሰራጩ ዜናዎችን ለቅሞ ትንታኔ በመስራት ቅድመ መረጃ ማቅረቡን አመልክቷል። ያቀረባቸውና የጠቅሳቸው መረጃዎች እውነተኛ ለመሆናቸው ማስረጃ ግን የለውም። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰብሳሃራ አገራት ልቆ መሄዱን፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከምስራቅ አፍሪቃ መሪ መሆኗን ጠቅሶ የጸጥታ ችግር ስላለ በሚል ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ይሰብካል።
ይህ በአገር ልጆች ጭምር እየተመራ እንደሆነ ፍንጭ የወጣበት ሪፖርት ምርመራና የስጋት ቅድመ ትንተና ዋናው የስራው የጀርባ አጥንት እንደሆነ ይናገራል። ተቋም ከስያሜውና ለራሱ ከሰጠው የነብይነት አክሊል ውጪ ሌላ ዝርዝር የማንነት መገለጫ ስለሌለው ጥሞናን ለሚያስቀድሙ ዜጎች ሁሉ “ ማንህ ነብዩ፣ እነማን ናችሁ ትንቢት አብሳሪዎቹ? ወዘተ” የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።
በዓለም የሚታወቁ የመብት ተሟጋች ነን ባዮች፣ የቀውስ ተንታኞች፣ እንደ ሂዩማንራይትስ ዎች፣ ክራይስ ግሩፕ፣ አምነስቲ፣ ጄኖሳይድ ፎረምና የመሳሰሉት ዓላማቸው ምንም ይሁን ምን ማንነታቸውን አይደብቁም። ለሚያወጡት ሪፖርት ከፊት ቆመው ሃላፊነት ይወስዳሉ። ማብራሪያና መከራከሪያም ያቀርባሉ። ይህ ራሱን ” ትንቢት ተናጋሪ” አድርጎ ያስቀመጠው ተቋም ወይም ማህበር ማንነት ምንም የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ፣ በተለይም በአፍሪቃ ቀንድ ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ሳብ ሳህራ ዘልቆ የሚሰራ መሆኑ፣ ትኩረት ሰትቶ የሚሰራባቸው አገራት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ መሆናቸው፣ በይፋ ባይጠቀሱም ስብስቡ ከነዚሁ አገር ላኩ ስፔሻል ፎርሶች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ የአካባቢውን ባህልና ወግ የሚያውቁ ናቸው መባሉ “ድርጅቱን ማን ነው የሚመራው” የሚለውን ጥያቄና “ለምን ዓላማ የህቡዕ ድርጅት እንዲሁን ተፈለገ?” የሚሉ ጉዳዮች በስፋት እነዲነሱበት አድርጓል።
ይህ በህቡዕ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ በርዕስ ከፋፍሎ ያወጣው ሪፖርት በየገጹ ከግርጌው ” ሚስጢራዊ ሰነድ” የሚል አርፎበታል። ይህ ህቡዕ ድርጅት ካልፈቀደ በስተቀር ሪፖርቱን ማባዘትም ሆነ ማሰራጨት ይከለክላል። ከስር የተወሰደው ስክሪን ሾት ሲሆን አንባቢያን ለትጎበኙት ግድ ነው። ኢትዮጵያ ላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮት እንዲገጥማት ሰይፉን ያነሳ ስብስብ ከጀርባ የሚነዳው ሃይል ስለመኖሩ ዝግጅት ከፍላችን በርካታ መረጃዎች እየደረሱት ነው። በተለይም ናይሮቢ የሚኖሩ ዜጎች ትብብር እየደረጉ ነው።
