የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ ደብዳቤና ፈቃድ ከተሰጠው ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ኤርትራ የሚያደርገው በረራ ሙሉ በሙሉ መታገዱን የሚያሳውቅ ደብዳቤ እንዲደረሰው መደረጉ እንዳስገረመው ገለፀ።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሐና አጥናፉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ወደ ኤርትራ በረራ እንዳያደርግ መታገዱን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲደርሰው ከመደረጉ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግና የመጫን አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ አውሮፕላኖችን እንዲጠቀም ተጠይቆ ነበር።
” በረራ እንድናቆም የሚጠይቀው ደብባቤ ከመድረሱ ከሁለት ሳምንት በፊት የምናደርገውን በረራ ከ10 ወደ 15 እንድናሳድግ፣ የምንጠቀመውን መለስተኛ አውሮፕላን ወደ ከፍተኛ አውሮፕላን እንድናሳድግ ፣ በቀን ሁለት በረራ እንዲሁም በየሳምንቱ ዓርብ ሦስት በረራ እንድናደርግ ጠይቀውን ነበር” ሲሉ ሐና ተናግረዋል።
አክለውም ፣ አየር መንገዱ በረራውን እንዳያሳድግ የሚጠይቅ ደብዳቤና ፈቃድ በተሰጠው በሁለት ሳምንት ውስጥ በረራውን እንዲያቆም የሚገልጽ ደብዳቤ ሲደርሰውና ይህም ባልተገባ መንገድ በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሰራጭ መደረጉ አስገራሚና አስደንጋጭ እንደሆነበት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እ.ኤ.አ. ከሴፕተምበር 30 ቀን 2024 ጀምሮ እንዲያቆም የሚያሳወቅ ደብዳቤ የደረሰው ቢሆንም፣ በረራውን እንዲያቆም የተወሰነበት ምክንያት በደብዳቤው ላይ አንዳችም ቦታ እንዳልተገለጸ የአየር መንገዱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል።
አክለውም ፣ በዛሬው ዕለትማለትም ሐምሌ 17 ቀን 2016 ዓም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እየተዘዋወረ የሚገኘው ደብዳቤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የተላከ ባለመሆኑ፣ በዚህ ደብዳቤ ላይ ለተዘረዘሩት ጉዳዮች ምላሽና አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ዙሪያ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ጋር ለመነጋገር እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል
ለሪፖርተር
ኤርትራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሥመራ የሚያደርገውን በረራ እንዲቋረጥ ወሰነች
በኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስቴር የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዛሬ በታተመው በመንግሥታዊው “ሓዳስ ኤርትራ” ጋዜጣ ላይ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ መታገዱን የገልጿል።
ባለሥልጣኑ በጋዜጣው ላይ ባወጣው መግለጫ መሠረት ከመስከረም 20/2017 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርጋቸው በረራዎችን በሙሉ ማገዱን አስታውቋል።
የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣኑ አየር መንገዱ እንዲታገድ የተወሰነው “ያልተገባ የንግድ ተግባራት” በመከተሉ ነው ሲል ወቅሷል።
የኤርትራ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ከደረሰባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ በአየር መንገዱ ተጓዦች ላይ “የተደራጀ እና ስልታዊ የሻንጣ ስርቆት” ይፈጸማል የሚለው ይገኝበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ተደጋጋሚ የበረራዎች እና የሻንጣዎች መዘግየት እንደሚያጋጥም ጠቅሶ፤ አየር መንገዱ ለተጓዦች ካሳ ሳይሰጥ ቆይቷል ብሏል።
ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውንጀላውን እንደማይቀበል እና የስም ማጥፋት እንደሆነ ጠቅሶ “በሰማነው ድንገተኛ ውሳኔ አዝነናል፣ በውሳኔውም ዙርያ ማብራርያ ለማግኘት ሙከራዎች እያደረግን ነው ያለ ሲሆን ጉዳዩም በበጎ መልኩ እልባት እንደሚያገኝ ያለውን ዕምነት ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት አስርት ዓመታት ቆይታ በኋላ ሀምሌ 11 2011 ዓ.ም ዳግም በረራ ወደ አስመራ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡
አዲስ ማለዳ