“ቀደም ሲል አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም” ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ። ለሶማሊያ ሰላም መከበር ወታደር ሲያዋጡ የነበሩ አገራት ስጋታቸውን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንዲረዱና የበኩላቸውን እርምጃ እንዲወስዱም አሳስቧል። በሶማሊያ እየሆነ ያለውን ሁሉ በንቃት በመከታተል ላይ እንደሆነም አመልክቷል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል፡፡
የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለዚሁ አዲስ ሽግግር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት፣ ቀጠናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል፡፡
በሁኔታው ላይ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ ወታደር ያዋጡ አገሮች ተደጋጋሚ ጥሪዎችና አስተያየቶች ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡
የመከላከያ ሠራዊታችንን መልካም ስምና ዝናን እንዲሁም መስዋዕትነት የሚያጠለሹ ተከታታይ መግለጫዎች ሲወጡ ኢትዮጵያ በዝምታ እንድታልፍ ከአንዳንድ ወገኖች በኩል ፍላጎት መኖሩ ይታያል፡፡
ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም፡፡ ይህም በመሆኑ በቀጣናው የብሄራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በንቃት እየተከታተለች ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገትና በክልሉ ያሉ ህዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋር ያለውን ወቅታዊ አለመግባባት ለመፍታት እንዲያስችል በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይም በንቃት ተሳትፎ አድርጋለች፡፡ በእነዚህ ንግግሮች ተጨባጭ ውጤቶችም ታይተዋል።
የሶማሊያ መንግስት እነዚህን ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡
በሶማሊያ ለማሰማራት የታቀደውን አዲስ የሰላም ተልዕኮ የማዘጋጀትና የመፍቀድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ በቀጠናው የሚገኙና ቀደም ሲል ወታደር አዋጭ የሆኑ አገራትን ተገቢ የሆኑ ስጋቶች ሁሉ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡
ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸውና ከንቱ አላማቸው ሲሉ በክልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞክሩ ኃይሎች ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸዉን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል፡፡
ቀደም ሲል አህጉራዊና አለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም።
ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ከሶማሊያ ህዝብና ከአለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል አሁንም ቁርጠኛ አቋም አላት፡፡
ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ፤ኢትዮጵያ