ቴሌግራም የተባለው የማኅበራዊ ትስስር መተግበሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፓቬል ዱሮቭ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ። ፓቬል በፈረንሳይ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው በፓሪስ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኝ አንድ አየር ማረፊያ ነው።ይህንኑ ተከትሎ “የምዕራባውያኑ ለሰብዓዊነትና ነጻነት ቆመናል የሚሉ ድርጅቶች የቴሌግራም መስራች ፓቨል ዱሮቭ እንዲለቀቅ ይጠይቃሉ” ሲሉ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ጠይቀዋል።
የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳለው ሥራ እስኪያጁ በቁጥጥር ሥር የዋለው ለ ቡርጌ በተሰኘው አየር ማረፊያ በግል አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ነው። ባለሥልጣናት እንዳሉት የ39 ዓመቱ ፓቬል በፖሊስ የተያዘው ከታዋቂው መልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ጋር በተያያዘ በተፈጸም ጥሰት በወጣበት የእስር ትዕዛዝ መሠረት ነው።
በሩሲያ የተወለደው ፓቬል የሩሲያ፣ የፈረንሳይ እና የአረብ ኤምሬትስ ጥምር ዜግነት ያለው ሲሆን ከ15 ቢሊዮን በላይ የተጣራ ንብረት እንዳለው ይገመታል።
በፈረንሳይ የሩሲያ ኤምባሲ ሁኔታውን ለማጣራት “አፋጣኝ እርምጃ” እየወሰደ እንደሆነ የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ቲኤኤስኤስ ዘግቧል። የፈረንሳዩ የተሌቪዥን ጣቢያ ቲኤፍ1 በድረ-ገፁ እንደፃፈው ፓቬል በግል አውሮፕላኑ ነበር ሲንቀሳቀስ የነበረው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ቢሊየነሩ የቴሌግራም መሥራች ከአዘርባይጃን ተነስቶ የመጣ ሲሆን በቁጥጥር ሥር የዋለው ደግሞ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2፡00 ነው። ግለሰቡ እሑድ ዕለት ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ሮይተርስ ፅፏል።
ሮይተርስ አክሎ ተሌግራም፣ የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር እና ፖሊስ እስካሁን ምንም ዓይነት መግለጫ አለመስጠታቸውን ዘግቧል።
ሩሲያ የተወለደው ፓቬል የሚኖረው የቴሌግራም ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ዱባይ ሲሆን የፈረንሳይ እና የዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ዜግነት አለው።
ፎርብስ የተባለው መፅሔት ፓቬል 15.5 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሀብት አለው ሲል ይገምታል።
ቴሌግራም የተባለው የመልዕክት መላላኪያ ገፅ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሩሲያ እና ዩክሬን እንዲሁም በቀድሞው የሶቪየት ኅብረት ሀገራት በጣም ታዋቂ እና በርካቶች የሚጠቀሙት መተግበሪያ ነው።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ፓቬል ዱሮቭ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለመንግሥት አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ ቴሌግራም በ2018 ሩሲያ ውስጥ ታግዶ ነበር።
ነገር ግን በ2021 ይህ ውሳኔ ተሽሮ መተግበሪያው ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል።
ቴለግራም ከፌስቡክ፣ ዩቲዩብ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዊቻት ቀጥሎ በጣም በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ማኅበራዊ ሚድያ ነው።
ቢሊየነሩ ፓቬል ዱሮቭ እና ወንድሙ ቴሌግራምን የመሠረቱት በአውሮፓውያኑ 2013 ሲሆን አሁን ቴሌግራም 900 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።
ፓቬል በ2014 ቪኮንታክቴ የተባለ ማኅበራዊ ሚድያው ላይ ያሉ ተቃዋሚዎችን ዝም እንዲያሰኝ ከሩሲያ መንግሥት የቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ ሞስኮውን ጥሎ ከወጣ በኋላ ማኅበራዊ ሚድያውን ሸጦታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዱሮቭን ፈረንሳይ ውስጥ መታሰረን በተመለከተ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ” ምላሳቸውን ውጠው ዝም ይላሉ ? ወይስ እንዲፈታ ይጠይቃሉ ? ” ብለዋል።
እ.ኤ.አ. በ2018 ሂዩማን ራይትስ ዎች ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፣ ፍሪደም ሃውስ ፣ ድንበር የለሽ ሪፖርተሮች እና ሌሎችን ጨምሮ 26 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሩስያ ፍርድ ቤት ቴሌግራምን ለማገድ የሰጠውን ውሳኔ አውግዘው እንደነበር ቃል አቀባይዋ አስታውሰዋል።
ዛካሮቭ ” አሁን ፓሪስ ደውለው የዱሮቭን መፈታት የሚጠይቁ ይመስላችኋል ? ወይስ ምላሳቸውን ውጠው ዝም ይላሉ ? ” ሲሉ ያሰራጩት በኦፊሳላዊ የቴሌግራም ቻናላቸው ነው።
ዛራኮቫ ፤ በ2018 ቴሌግራም ላይ የሕግ አውጭ ቅሬታዎች ነበሩ፣ ይህም በብዙ የኢንክሪፕሽን ሥርዓቱ ቴክኒካል መለኪያዎች ምክንያት ነው ሲሉ አስታውሰው ፤ ዱሮቭ ግን ነፃ ሆኖ መቆየቱን መተግበሪያውን ማሳገዱን ገልጸዋል።
የዱሮቭ በተያዘበት ቅፅበት በፈረንሳይ የሩስያ ኤምባሲ ጉዳዩን መከታተል እንደጀመረ ጠቁመዋል። ” የእኛን ዲፕሎማቶች ስለ ስራቸው ማስታወስ አያስፈልግም ” ሲሉም ዛካሮቫ አክለዋል።
ቴሌግራም ሩስያ እንዲሁም በዩክሬን አካባቢ እጅግ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለስልጣናትም ተመራጭ መልዕክት መለዋወጫ አድርገውታል።