መግቢያ
ወንጀል የማህበረሰብን ሰላም እና ደህንነት የሚያናጋ እንደመሆኑ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲታረሙ እንዲሁም ሌሎችም ከመሰል ድርጊት እንዲታቀቡ ወንጀል ፈፃሚዎች በህግ መጠየቃቸው የግድ ነው፡፡ ሆኖም ወንጀል ፈፃሚዎች በተለያየ የእድሜ ክልል የሚገኙ እንደመሆናቸው የሚታረሙበት መንገድ እና የሚወሰደው የእርምት እርምጃ ይህን ያገናዘበ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም በአዋቂዎች እና በታዳጊዎች ላይ የሚወሰኑ ቅጣቶች እና የእርምት እርምጃዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ ስለወጣት ወንጀል አድራጊነት ምንነት እና ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ የሚወሰዱባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎ እንዳስሳለን፡፡
የወጣት ወንጀል አድራጊነት ምንነት
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ አንቀፅ 52 እና ተከታዮቹ መሰረት በሀገራችን የወንጀል ተጠያቂነት የሚጀምረው ከ9 አመት ጀምሮ ነው፡፡ በመሆኑም 9 አመት የሞላው ልጅ ወንጀል ውስጥ ገብቶ ቢገኝ የወንጀል ተጠያቂነት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ እድሜያቸዉ ከ9-15 ዓመት የሆናቸዉ ልጆች ወንጀል ፈፅመው ቢገኙ የሚወሰዱባቸው የእርምት እርምጃዎችም ከመደበኛ ቅጣት የተለዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ብቻ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እድሜያቸዉ ከ15 አመት በላይ የሆነ ነገር ግን 18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣት ልጆች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ቢሆንም ወንጀል ፈፅመው ከተገኙ ፍርድ ቤት በልዩ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ሚያስገባቸው ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው በወንጀል ህግ የተመለከቱ መደበኛ ቅጣቶች ይፈፀሙባቸዋል፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታ የጥንቃቄ እርምጃ የሚወሰድባቸው ወጣት ወንጀል አድራጊዎች እድሜያቸው ከ9 እስከ 15 አመት ያሉ ልጆች ናቸው፡፡
ወጣት ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ የሚፈፀሙ ሥነ-ሥርአቶች
የወጣት ወንጀል አድራጊዎችን በተመለከተ ተፈፃሚ የሚሆነው ሥነ ሥርአት ከአዋቂ ወንጀል ፈፃሚዎች የተለየ ነው፡፡ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ወንጀል ውስጥ ገብተው ሲገኙ ወዲያውኑ አቅራቢያው ወደሚገኝ ፍ/ቤት እንዲቀርቡ መደረግ አለበት፡፡ ከቀረቡም በኋላም ያቀረባቸው አካል ወይም ፖሊስ የወንጀሉንና የምስክሮቹን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ እንዲገልፅና አስፈላጊ በሆነ ጊዜም አቤቱታ እንደደንቡ መሠረት እንዲያቀርብ ይጠበቃል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቀረበውን ከመዘገበ በኋላ ፖሊስ ምርመራውን የሚፈፅምበትን ሁኔታ የሚገልጽ መምሪያ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ከወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 172/1/ እና /2/ ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣት ወንጀል አድራጊን በተመለከተ እንደአዋቂ በመደበኛ ምርመራ እና ክስ ሂደት ሳይሆን አቤቱታው ቀጥታ በፍርድ ቤት ክትትል ስር የሚታይ ነው፡፡ ሂደቱም ከመደበኛው ሂደት ተለየ ነው፡፡ ይኸውም፡-
- የተያዘ ሰው በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ አቅራቢያው ፍርድ ቤት የመቅረብ ሕገ-መንግስታዊ መብት ያለው ሲሆን ወጣት ወንጀል አድራጊን ግን በወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 172(1) መሰረት ፖሊሱ፣ ዐቃቤ ህጉ፣ ወላጁ ወይም ሞግዚቱ ወዲያውኑ እንዲያቀርበው ይጠበቃል፡፡
- በመርህ ደረጃ ማንኛውም የተከሰሰ ሰው ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመሰማት ሕገ-መንግስታዊ መብት አለው፡፡ የተከራካሪውን የግል ሕይወት፣ የሕዝብ ሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ይከናወናል፡፡ በወጣት ወንጀል አድራጊዎች የወንጀል ፍትህ ሥርአት ውስጥ ግን ነገሩ በሙሉ የሚሰማው በዝግ ችሎት ውስጥ እንደሆነ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 176/1/ ላይ ተመልክቷል፡፡
- የወጣት ወንጀል አድራጊዎች ጉዳዮች በሙሉ መደበኛ ባልሆነ አካሄድ እና መግባባት በሰፈነበት ድባብ መካሄድ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ከወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 176/2/ ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣቱ ሀሣቡን በነፃነት እንዲገልፅ መፍቀድ፣ በጥሞና ማዳመጥ፣ ክፍት የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዳለበት ያሳያል፡፡
- የወጣት ወንጀል አድራጊዎቹ ወላጅ ወይም ቤተዘመድ ባልተገኙ ጊዜ ወይም እነሱም ቀርበው ወጣቱ ከ1ዐ ዓመት በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል በተከሰሰ ጊዜ ፍ/ቤቱ ጠበቃ ሊመድብለት እንደሚገባ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 174 ላይ ተመልክቷል፡፡
- ወጣት ወንጀል አድራጊው ሊሰማው የማይገባ ነገር በማስረጃነት የቀረበ ወይም ትችት የሚሰጥበት በሆነ ጊዜ ሊሰማው የማይገባው ነገር በሚነገርበት ጊዜ ከችሎቱ ክፍል እንዲወጣ የሚደረግ ስለመሆኑ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 175 ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡
ችሎቱ በሚካሄድበት ጊዜም የቀረበው አቤቱታ ወይም ክስ ማመልከቻ ለወጣቱ ተከሣሽ ተነቦለት እንዲረዳው መደረግ አለበት፡፡ ክሱን ሙሉ ለሙሉ ያመነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በወ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 176(4) መሰረት ወዲያውኑ የጥፋተኝነት ውሣኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ወጣት ተከሣሽ አቤቱታውን ወይም ክሱን ያላመነ እንደሆነ ለአቤቱታው ወይም ለክሱ የመጡትን ምስክሮች ፍ/ቤቱ ይጠይቃል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን በጥያቄ ከመረመረ በኋላ በተከሳሹ በኩል መስቀለኛ ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ወጣቱ ወይም እንደራሴው ወይም ጠበቃው ማንኛውም ምስክር እንዲጠራለት ማድረግ ይችላል፡፡ ከእነዚህ ሂደቶች መረዳት እንደሚቻለው አንድ ጊዜ አቤቱታውን ካቀረበ በኋላ አቤቱታውን ወይም ክሱን ደግፎ ክርክር የሚያደርግ ተከራካሪ ወገን ወይም ዐቃቤ ህግ የማይገባ መሆኑና ፍርድ ቤቱም ራሱን እንደከሣሽም እንደ ዳኛም በመሆን ሂደቱን እንደሚመራ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም ወጣት ወንጀል አድራጊዎች በክሱ ጥፋተኛ ሆነው ያልተገኙ እንደሆነ ፍ/ቤቱ ወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 177/1/ መሰረት ወዲያውኑ በነፃ መልቀቅ አለበት፡፡ ይሁንና ወጣቶቹ በክሱ ወይም አቤቱታው ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ እንደሆነ ለወጣቶቹ የሚጠቅም ውሣኔ ለመስጠት እንዲያስችለው ስለወጣቶቹ ጠባይና ስለቀድሞ ጥፋት ለመጠየቅ ማንኛውንም ድርጅት፣ ማንኛውንም ሰው ወይም እንደራሴ ፍርድ ቤቱ መጥራት ይችላል፡፡ በፍርድ ቤቱ የተጠሩት ሰዎች ቃል ከተሰማ በኋላ የወጣቶቹ ወገን መልስ መስጠትና ስለጠባዩ ምስክሮች መጥራት ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹን ከጠየቀ በኋላ የከሣሽ ወገን ስለቅጣቱ በቃል እንደሚያመለክት በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 177/2/ እና /3/ ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶችበወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች ግብ ወጣቶቹን ከገቡበት የተሳሳተ መንገድ እንዲወጡ እና መልካም ዜጎች ሆነው ጥሩ አስተሳሰብን እንዲያዳብሩ ከዚያም ሠላማዊና ለሕግ ተገዥ የሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ የመፍትሄ እርምጃዎች በወንጀል ህጉ አንቀፅ 158-168 የተመለከቱት ብቻ እንደሆኑ በአንቀፅ 53 ተደንግጓል፡፡ እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች ምንም አይነት የቅጣት ይዘት ሳይኖራቸው የወጣቶቹን መመለስ አላማ ያደረጉ እርምቶች ናቸው፡፡ እነዚህም፡-
- ለአካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ጥፋተኛ ህክምና የሚያስፈልገው ሲሆን በተለይም የአዕምሮ ደካማነት፣ የአዕምሮ እድገቱ የዘገየ፣ አዕምሮው የታመመ፣ የሚጥል በሽታ ያለበት፣ በአልኮል ሱሰኝነት የተጠመደ ወይም በናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ ነገሮች ወይም በሌሎች የሚያፈዙ እፅዋት የተመረዘ ሆኖ ሲገኝ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 158 መሰረት ፍርድ ቤት ተገቢ ወደ ሆነው የህክምና ተቋም እንዲሄድ ሊያዝ ይችላል፡፡ በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ወጣት ወንጀል አድራጊው ወደህክምና ተቋም የሚላክ ከሆነ ከህክምናው ጋር ትምህርት እና ስልጠና እንዲካተት ሊያደርግ ይችላል፡፡ የህክምና ጊዜው የተላከበት የህክምና ባለስልጣን ወይም ባልደረባ ያስፈልጋል እስካለው ድረስ የሚቆይ ይሆናል፡፡
- ለአካለመጠን ያልደረሰው ወንጀል አድራጊ አስተዳደጉ በጎ ካልነበረ፣ በንዝህላልነት የተተወ ወይም ጠባዩ ወደመጥፎ ስራ ያዘነበለ ወይም የሚያዘነብል ሲሆን በወንጀል ሕግ አንቀፅ 159 መሰረት በጠባቂ ስር ሆኖ ቁጥጥር እየተደረገበት ትምህርት እና አስተዳደግ እንዲያገኝ ይታዘዝለታል፡፡ ጠባቂ የሚሆኑ ዘመዶች ከሌሉት ወይም ዘመዶች ኖረው ችሎታ የሌላቸው እንደሆነ ብቁ ለሆነ ሰው ወይም ህፃናትን ለመጠበቅ እና ለመቆጣጠር ለተቋቋመ ድርጅት እንዲሰጥ ያዛል፡፡ ይህ በሆነ ጊዜ ተረካቢዎቹ ሀላፊነታቸውን ተከታትለው የሚያስፈፅሙ ስለመሆኑ ፍርድ ቤት ቀርበው በፅሑፍ በማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ወደ ትምህርት ቤት አዘውትሮ እንዲሄድ፣ ወይም የሙያ ስራን እንዲለምድ፣ ከአንዳንድ ሰዎች ከመገናኘት ወይም ከአንዳንድ ስፍራ ከመድረስ እንዲከለከል፣ በተወሰኑ ጊዜያት ከጥበቃ ባለስልጣኖች ፊት እንዲቀርብ ወይም ሪፖርት እንዲያቀርብ እና የመሳሰሉ ግዴታዎች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡ ጠባቂዎቹ የተጣለባቸውን የማሳደግና የማስተማር ሀላፊነት ካልተወጡ ፍርድ ቤቱ የጠባቂነት ስልጣናቸውን የሚወስድባቸው ይሆናል፡፡
- ፍርድ ቤት ተገቢ መስሎ በታየው ጊዜ ለአካለ መጠን ያልደረሰውን ልጅ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 160 መሰረት መውቀስ ወይም መገሰፅ ይችላል፡፡ ወቀሳውም ለአካለ መጠን ያልደረሰው ወንጀል አድራጊ የፈፀመውን የወንጀል ድርጊት እንዲረዳው እና ለወደፊት ከእንዲህ አይነቱ ተግባር እንደቆጠብ በጎ ተግባር እና መልካም ፀባይ ለማምጣት ያለመ መሆን ይኖርበታል፡፡ ፍርድ ቤት በወቀሳ እና በተግሳፅ የሚያልፈው የወንጀሉን ቀላልነት እና የወንጀል ፈፃሚውን የመረዳት ችሎታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ግን ከሌሎች የጥንቃቄ እርምጃዎች ጋር ተጣምሮ ሊተገበር ይችላል፡፡
- በትምህርት ቤት ወይም በመኖሪያ ቤት ተወስኖ እንዲቆይ በወንጀል ሕግ አንቀፅ 161 መሰረት ትዕዛ ሊሰጥ የሚችል ሲሆን ይህም የሚደረገው ፍርድ ቤቱ ወጣት ወንጀል አድራጊው በቀላሉ የሚታረም መስሎ ከታየው እና የሚቆይበትን ጊዜ በመወሰን እና በእረፍት ጊዜው የሚያከናውነውን ተግባር በመስጠት ነው፡፡
- የወጣት ጥፋተኛው የቀድሞ ታሪኩን፣ ፀባዩን እና መጥፎነቱን እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነት እና አፈፃፀሙን በማየት በወንጀል ህግ አንቀፅ 162 መሰረት ወንጀል አድራጊዎችን ለማረሚያ እና ለማስተማሪያ በተቋቋመ ተቋም እንዲገባ ፍርድ ቤቱ ሊያዝ ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት ወጣት ጥፋተኛው ጠቅላላ ትምህርት፣ ግብረገብነት፣ የመተዳደሪያ ልዩ ሙያ የሚያገኝበትን (ልዩ መልመጃ) እንዲሁም ወደማህበራዊ ኑሮው እንዲመለስና በቅንነት እየሰራ እንዲኖር አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉ እንዲማር ያደርጋል፡፡
- በዚህ መልኩ ሚሰጥ ትእዛዝ የሚቆይበት ግዜ መገለፅ ያለበት ሲሆን ቢያንስ አንድ አመት ቢበዛ አምስት አመት እንጂ ለአካለመጠን ከደረሰ በኋላ ተፈፃሚነት የለውም፡፡
ፍርድ ቤቱ መርጦ የወሰነው የጥንቃቄ እርምጃው የማያስተምር አይነት ከሆነ መለወጥ ይችላሉ፡፡ የእርምት እርምጃ ተፈፀመው ውጤት አልባ ሆነው ሲገኙ የእስራት ወይም የመቀጮ ቅጣት ተፈፃሚ የሚሆኑ እንደሆነ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 166 ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡
በአጠቃላይ እድሜያቸው ከ9 አመት እስከ 15 አመት የሚሆኑ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ወንጀል ፈፅመው የእርምት እርምጃ ሲጣል ውሳኔ ሰጪ አካላት በዋነኛነት ማስተማርን እና በሂደትም ከቤተሰብና ከማህበረሰቡ ጋር የተሳካ ውህደት ፈጥረው መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግን አላማው ያደረገ መሆን ይኖርበታል፡፡ በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የፍትህ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር