ቀደም ሲል በኢህአዴግ ዘመን የዩኒቲ ዩኒቨርስቲን ሸጠው ወደ አሜሪካ የሸሹት ዶክተር ፍስሃ እሸቱ በለውጡ ማግስት ወደ አገር ቤት የመመለስ እድል ካገኙ ዜጎች መካከል አንዱ ናቸው። የንግድ አሳብ በማመንጨት፣ አዲስ ፕሮጀክት በመጀመር ግን ባለመጨርሰ ወይም ገፍቶ ባለመሄድ የሚታወቁት እኚሁ ሰው አዲስ አበባ በገቡ በአጭር ቀን ውስጥ “ፐርፐዝ ብላክ” የሚባል ድርጅት ከፍተው የሚዲያ ቀልብ ስበው ነበር።
መጀመሪያ አሜሪካ እንደገቡ በስድስት ወር የወያኔን መንግስት ለመጣል የሚያችል የሽግግር መንግስት አቋቁማለሁ ብለው የዲያስፖራውን ወኔ ወዘወዙት። በወቅቱ ኢህአዴግ እንኳን ሊወድቅ ወዘወዝ ሊያደርገው የሚችል አንዳችም ነገር ባልነበረበት ወቅት እሸቱ ተነስተው በሸንጎ እንደሚያስወግዱት ሲናገሩ አጨብጫቢው ብዙ ነበር።
ቆም ብሎ መጠየቅ የማይችለውና የተሰጠውን በመጋት የሚታወቀው ዴያስፖራ አዳራሽ እየሞላ አጨበጨበ። እሸቱ ቀስ በቀስ ሞቅታቸው ለቀቃቸውና በዛው ጠፉ። ኢህአዴግ ውስጥ የተነሱ የውስጡ አርበኞች ለውጡን በየአቅጣጫው ኔት ወርክ መስርተው እውን ሲያደርጉት፣ እሸቱ “ብላክ ፐርፐዝ” የሚባል አስደንጋጭና አስገራሚ ስያሜ መርጠው አዲስ አበባ ከች አሉ።
ከዕርሻ ግብአት ጅመሮ በአስገራሚ ዋጋ የቤት ባለቤት የሚያድርግ አዋጅ ይዘው የተነሱት ዶክተር ፍስሃ መጀመሪያው ላይ አሳባቸውን የሚያደንቁ ጎረፉላቸው። በሚሊዮኖች ሰበሰቡ። ከጅምሩ ” መጀመር እንጂ መጨረስ መች ያውቁበታል” በሚል ስጋታቸውን የገለጹ ነበሩ። እያደር ይህ አሳብ ገዢ እየሆነ ሲመጣ በሚዲያ መዋከብና መሞገት የዕለት ተዕለት ስራቸው ሆነ።
የብላክ ፐርፐዝ የማስታወቂያ አዋጅ ሚዲያውን ከማነቃነቅ አልፎ የተኛውን መንግስት ቀሰቀሰ። እሳቸውም አደባባይ እየወጡ በአንድ ሚሊዮን ብር የተንጣለለ ቤት እንደሚያስረክቡ መናገራቸውን ገፉበት። ነገሩ እየከረረ ሄዶ አንዳንድ ህጋዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እርስዎን አምኜ ነው ወደ አገር ቤት የገባሁት ጩኸቱን ዝም አሰኙልኝ” ዓይነት ጥሪ አሰምተው፣ ሲነጋ እንደወትሮው አሜሪካ ተገኙ። እሳቸው በሌሉበት፣ ባልደረቦቻቸው ተያዘው ክስ ተመሰረተባቸው። ክሱ ይህን ይመስላል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ የቦርድ አባልና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሐ እሽቱን (ዶ/ር) ጨምሮ በ10 ግለሰቦችና ሁለት ድርጅቶች ላይ ክስ መስርቷል። ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ
1ኛ የፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ የቦርድ አባልና ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሐ እሽቱ (ዶ/ር)፣
2ኛ የተቋሙ ም/ስራ አስፈጻሚ ኤርሚያስ ብርሃኑ (ዶ/ር)፣
3ኛ የተቋሙ ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር እና የቦርድ አባል ወ/ሮ ኤፍራታን ነጋሽን ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ግለሰቦች እንዲሁም ፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ እና ኖትር ዲዛይን ሃ/የተ/የግ/ማህበር ናቸው፡፡
- በአዲስ አበባ ከተማ መሃል ሜክሲኮ ላይ በ100 ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ባለ 3 መኝታ ቤት መኖሪያ ቤት በ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚሸጥ መሆኑን በሚዲያ በማስተዋወቅ ሰዎች ቤት ለመግዛት ሲሄዱ “መጀመሪያ ገንዘቡን አስገቡና ውሉን ትመለከታላችሁ ” በማለት ከሌሎች ግብረዓበሮቻቸው ጋር በመሆን አሳሳች ቃላቶችን በመጠቀም፣
- ሰዎች ገንዘቡን ካስገቡ በኋላ ደግሞ የአክሲዮን ግዢ ውል እንዲፈርሙ በማድረግ ምንም አይነት የግንባታ ቦታ ባልተረከቡበት ሁኔታ 2 ቢሊየን 234 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በመሰብሰብ፣
- ቤቱን ሰርተው ሳያስረክቡ በመቅረት
- ግማሹን ገንዘብ ወደ ውጭ እንዲሸሽ በማድረግ፣
- ኮሚሽን በመቀበልና በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው በአዲስ አበባ ፖሊስ በኩል በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የምርመራ ማጣሪያ ሥራ ሲከናወን ነበር።
በዚህ መልኩ ፖሊስ ሲያከናውነው የቆየው የምርመራ ማጣሪያ ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ዐቃቤ ሕግ ተደራራቢ ዝርዝር ክሶችን በየደረጃቸው አቅርቦባቸዋል።
ከቀረቡ ክሶች መካከል በአንደኛው ክስ ላይ ከ1ኛ – 9ኛ ባሉ ተከሳሾች ላይ እንደተመላከተው በኢፌዲሪ የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) እና (ለ) እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ ይገኝበታል።
እንደ አጠቃላይ በቀረበው ተደራራቢ ክስ ዝርዝር ችሎት ለቀረቡ 4 ተከሳሾች ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን የተከሳሾቹ ጠበቆች በደንበኞቻቸው ላይ የቀረበውን ክስ ዝርዝር ተመልክተው ዋስትና ላይ ክርክር ለማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ዋስትና ላይ የሚደረገውን የግራ ቀኝ ክርክር ለመከታተል ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ተዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾችን ፖሊስ በአድራሻቸው አፈላልጎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መስጠቱን ኤፍቢሲ ዘግቧል። ፍስሕ እሸቱ (ዶ/ር) ኮብልለው አሜሪካ መግባታቸው ይታወሳል።