” … ሃሳቤን የሰጠሁት ባለኝ ኃላፊነት መሰረት ነው። ማንንም አላጠቃሁም። አላነሳሁም። ቴክኒካል ጉዳይ አንስቼ ነው የተናገርኩት። በግል ወስነሻል ስለተባልኩበት ጉዳይ ምላሽ አቅርቢያለሁ …ብላናለች። ምንም ይሁን ምን የአንድን የዓለም ዓቀፍ፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ጀግና፣ ትልቅ ህዝባዊ ተቋም መሪ ድምጽ ማፈን በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከተራው የመናገር መብት ባሻገር የሚታዩ ወቅታዊ ጉዳዮችም ይኖሩበታል። ባለን አግባብና ዕውቂያ ለታላላቅ ተቋማትና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ይፋ እናደርጋለን። ኢቲቪም ጥቁር ታሪክ ይጻፍለታል ….
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ባለስልጣናት በወረደ ትዕዛዝ ድምጿ መታፈኑን ቅሪታዋን የገለጸችላቸው ወገኖች አስታወቁ። የአንድ አገር ብሄራዊ ቴሌቪዥን በዚህ ደረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ሲነዳ ማየት አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ዜናውን የሰግጡን ክፍሎች አመልክተዋል።
ሻለቃ ደራርቱ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን መምራት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ፓሪስ ኦሊምፒክ ድረስ በሁሉም አግባብ ቃለ ምልልስ አድርጋ ነበር። አንድ ሰዓት ከስምንት ደቂቃ የፈጀው ቃለ ምልልሷ በተለይም በፓሪስ ኦሊምፒክ በተነሱ ቅሬታዎችና ችግሮች ዙሪያ የተሞገተችበት እንደነበር ስለ ቃለ ምልልሱ የሰሙት ገልጸዋል።
እሷን በሚመለከታት ጉዳይ፣ በተለይም በግሏ ወስናለች ተብላ በተወቀሰችበት የአትሌት ጉድፋይ ሶስት ውድድሮችን እንድትወዳደር የተፈቀደበት አግባብ፣ እንዲሁም አጠቃላይ በአትሌቲክሱ ውጤት ዙሪያ ዝርዝር መረጃ የሰጠችበት ቃለ ምልልስ ተጠናቆ ለስርጭት ከተዘጋጀ በሁዋላ ነው የታገደው።
በየትኛውም የአገሪቱ ፍርድ ቤትም ሆነ ህጋዊ ተቋማት ገድብ ያልተጣለባት፣ በግለሰቦችም ይሁን በቡድን ደረጃ የወነጀለችው አካል በሌለበትና አንድን ትልቅ ህዝባዊ ተቋም እንደሚመራ ታዋቂ የአገር ጀግና የሻለቃ ደራርቱን ቃለ ምልልስ ማገት ዝም ሊባል የሚገባው ጉዳይ እንዳልሆነ ዜናውን ያጋሩን ገልሰዋል።
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በእነ ኃይሌ ገብረስላሴ መካከል የተፈጠረውን የስልጣን ውክልናና የጉባኤ አካሄድ ብዙም አደባባይ ሳይወታ ቆይቶ እንደነበር ይታወስል። ጉዳዩ ሰፊ የንትርክ አጀንዳ ሆኖ መሰማት የጀመረው የፓሪስ ውድድር ሲቃረብ ነበር። ይህንኑ ተከትሎ በዘመቻ በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ አጋቦች ከፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ጋር አብሮ እንዲጀመር የተደርገው ውዝግብ ተወዳዳሪ አትሌቶች ላይ የተፈጠረው የስነ ልቦና ጫናና ውጥረት ጥቁር በኦሊምፒክ መድረክ የተመዘገበ ጥቁር ጠባሳ ሆኖ አልፏል።
ችግሩን አስቀድም ወይም ከኦሊምፒክ ውድድሩ መጠናቀቅ በሁዋላ በሚፈለገው መልኩ ማጉላት ይቻል እንደነበር የሚናገሩ ወገኖች ልክ አሁን በህግ ለማስኬድ እንድተሞከረው በጨዋነት ማካሄድ ይቻል እንደነበር አስቀድመው አስታውቀው ነበር።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የማህበራዊ ሚዲያው ሰላባ እንደሆነ የሚነገርለት ኢቲቪ የደራርቱን ቃለ ምልልስ ያፈነው ምን አልባትም ህዝብ በግርድፍ ሲደርሰው የነበረውን፣ ምን አላባትም ህዝብ ሆድ እንዲብሰው ተደርጎ እየተቀነጫጨበ ሲተላለፉ የነበሩ መረጃዎችን ሙሉ መረጃ በመስጠት ሊያተራ ይችላል ከሚል ስጋት ሊሆን እንደሚችል ግምት አለ።
በፍርድ ቤት ዜና ሳይቀር የአንዱን ወገን ዘግቦ ሌላው ላይ በር የመዝጋት አካሄድ እንዳለ ቀደም ሲል ተበድለን ያሉ ወገኖች ማስታወቃቸው ይታወሳል። “ኢቲቪ የግብር ከፋዩ ህዝብ እንጂ የተወሰኑ ባለስልጣናት መናኛ መድረክ አይደለም” የሚሉት የደራርቱ ቅርብ ወገኖች ሌሎች የቴሊቪዥን ጣቢያዎች ስለ መናገር ነጻነት ሲሉ ለሻለቃ ደራርቱ መድረክ እንዲሰጡ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ብሮድካስት ኔትዎርክ ለሻለቃ ደራርቱ በማንኛውም ጊዜ ደጁ ክፍት እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን መረጃ ያደረሱ አስታውቀው፣ ኢቲቪ ሻለቃ ደራርቱን የሚያክል የዓለም ዕውቅና የአገር ባለውለታ አትሌት ድምጽ ማፈኑ በታሪክ እንደሚመዘገብ አመልክተዋል። አያይዘውም ለተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው እንደሚያስታውቁ ገልጸዋል። አፈናውንም ከተራውና ተፈጥሯዊው የመናገር መብት አሻግረው እንደሚያዩ ገልጸዋል።