ከትግራይ ሁለት ወገኖች ሁለት ዓይነት ድምጾችና ጥሪ እያሰሙ ነው። መንግስት በበኩሉ ዝምታን መርጧል። ጥሪውን የሚያሰሙት ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ የሚወነጃጀሉ፣ አንዱ ሌላውን ” የወርቅ ኮንትሮባንዲስት፣ ከሻዕቢያ ጋር የምታመቻምች” ሲለው ሌሎቹ ደውግሞ ” ከሃዲ” በማለት ለነቀፌታው ምላሽ የሚሰጡ ናቸው። ጥሪዎቹን የሚሰሙ፣ ጥሪውን ከሚያሰሙት ወገኖች ቁመናና ጀርባ በመነሳት የተለያዩ አስተያየቶች እየሰጡ ነው።
እርግጥ ነው በትግራይ ከመንግስት ጋር ተስማምቶ መስራት የሚፈልግ ቡድን አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ኡህን ቡድን ” ከሃጂ” በማለት የመደበና ከሻእቢያ ጋር ግንኙነት የጀመረ ቡድን አለ። በተመሳሳይ ከነ ትጥቁ ቁጭ ያለ ሰፊ ወታደራዊ ኃይል የሚመሩ አሉ። ከወታደራዊ አመራሮቹ መካከል በወርቅና የከበሩ ማዕድናት በኮንትሮባንድ ንግድ በኤርትራ በኩል የሚያሳልጡ ኧንዳሉ በመረጃና ማስረጃ መረጃ እየወጣ ነው።
በዚህ መካከል ነው ከትግራይ የአገር መከላከያ ወደ ትግራይ ሊገባና ልክ እንደቀድሞው ከኤርትራ ጋር የሚጋራውን ድንበር እንዲጠብቅ ጥሪ እየቀረበ ያለው። ጥሪውን “በፍጹም” በማለት የማይቀበሉና ቀደም ሲል የትህነግ ኃይሎች በመከላከያ ላይ የፈጸሙትን ሊደግሙት እንደሚችሉ፣ ለስልት ሲባል መከላከያ ከባድ መሳሪያ ታንክና መድፍ ይዞ እንዲገባ፣ የአየር ኃይሉ ተዋጊ ጀቶችን እንዲያቀርብ እንደተፈለገ የሚናገሩ ነገሮች ሳይጠሩ መንግስት እዚህ ጨዋታ ውስጥ መግባት እንደሌለበት ይወተውታሉ።
ሌሎች ወገኖች ድንበር የመጠበቅ ግዴታ የመንግስት ነውና ሻዕቢያ የትግራይን 58 ቀበሌዎች ወሮ መንግስት ዝም ሊል አንደማይገባው ጠቅሰው ይወቅሳሉ። “የዜጎቹን ስለማ መጠበቅ የማይችል መንግስት” ሲሉም አቅሙን ያሳንሱታል። በቀጥታ ለወቃሾቹ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን ተያያዥ ጥያቄ ቀርቦላቸው ” ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ለማለት ነው – በአልጀርሱ ስምምነት ከተጠቀሰው ውጭ የተያዘ ቦታ ካለ አግባብ አይደለም እንዲለቁ እንነጋገራለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ፓርላማ ላይ መመለሳቸው ይታወሳል። ይህ የሰሙ እንግዲህ የችግሩ ጥንስስ አቶ መለስ መሆናቸውን በመጥቀስ ዓመታትን ወደ ሁዋላ ተመልሰው የአልጀርሱን ስምምነት ቅጥፈት ሳይቀር ሲተነትኑ ተሰምቷል። መንግስት ከሻእቢያ ጋር አሸሼ ገዳሜውን ካቆመ በሁዋላ ይህ መባሉ ሁለቱም እንደማይፈላለጉ አመላካች ነበር ተብሎም ነበር። ግን አይመስልም።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወቂ ዛሬ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በእጅጉ እንደሚፈሩ አዲስ አበባ ለስራ ተልኮ ወደ ዱባይ ያቀናው የሻዕቢያ በሳስ ወይም ሰላይ ለኢትዮሪቪው መረጃ ሰጥቷል። በተመሳሳይ ትህነግ ወታደራዊ አቅሙ ሳይሟሽሽ ልባቸውን ከፍተው በህብረት ለመስራ እምነት የላቸውም። እንደ በሳሱ ድምዳሜ ይህ ስጋታቸው ነው ኢሳያስን ወደ አማራ ክልል የወሰዳቸው።
“Ethiopia and Eritrea Have a Common Enemy” ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጠላት እንዳላቸው በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ብሮንዊን ብሩቶን በሰፊ ትንተናቸው ለውጡ ሰሞን ጽፈው ነበር። በጁላይ 2012 እኚሁ ጸሃፊ በሰፊው ሃተታቸው ኢትዮጵያና ኤርትራ የጋራ ጠላታቸውን ካስወገዱ በሁዋላ በዕኩል ፍጥነት ካልሄዱ አብረው ለመቀጠል እንደሚችገሩም አስቀድመው የስጋት ትንተናም አኑረው ነበር። (የጋራ ጠላት ከሳቸው በቀጥታ ጥሬ ትርጉም የተወሰደ ነው) አንዳቸው በጎማ አንዳቸው በቸርኬ ከተጓዙ ወዳጅነቱ እንደማይቀጥል በግልጽ አመልክተዋል። ይህን ሲሉ ኤርትራ በያዘችው መንገድ መቀጠል እንደማትችል ሲያሳስቡ ነበር። እዚህ ላይ ደግሞ የአገራቸው አሜሪካ ፍላጎት እንደሚጎላ እሙን ነው። ይህን ለማስታወስ ያህል ነው።
የሻዕቢያ መሪ ኢሳያስ አፉወርቂ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መሪነት በሚወሰድ እርምጃ ሳቢያ ንግስናቸው እንደሚያበቃ በኦሮሞ የተቃዋሚ ድርጅት አመራርነት ለረዥም ጊዜ የቆዩትና አሁን ላይ ወደ ማማከር የዞሩት ፖለቲከኛ ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት በኢሳያስ ዘንድ ኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱትን ፖለቲካ የሚቀይር አንድ ይሄ ነው የሚባል የአመለካከት ለውጥ እስካላደረጉ ድረስ መወገዳቸው የኢትዮጵያ አሁናዊ አጀንዳና የብሄራዊ ጥቅሟ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ይህንን ኢሳያስ ከማንም በላይ ያውቁታል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኢትዮጵያን አየር ኃይል ሲጎበኙ (ያላዩት እንዳለ ሆኖ) “ይህ ሁሉ ከመቼው? ለማን ነው? ” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን እንደመታከክ ብለው መተየቃቸውን መስማታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪ፣ አማራ ክልል ጦርነት ባይጀመር ኖሮ ነገሩ ሁሉ ይህኔ ታሪክ ሆን ሊቀር እንደሚችል፣ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የማይቀር እንደሆነ እምነታቸው ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዝግጅትና አቋም የኢትዮጵያን ጥቅም ለሚጻረሩ ሁሉ አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት በሚችልበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲናገሩ መደመጡ ከላይ የተሰጠውን አስተያየት ያጎላዋል። እሳቸው እንዳሉት የኢትዮጵያ ዝግጅት በቲክኖሎጂም፣ ሆነ በአፈጻጸም ደረጃ የላቀ ነው። በዚሁ አንደበታቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቅርቡ ከአፍሪካ መሪ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትላቸው ጀነራል አበባው ታደሰ በተደጋጋሚ፣ በተለያዩ ታላላቅ መድረኮች ” መከላከያ የሚዘጋጀው በየመንደሩ ለሚሹለከለኩ ተላላኪዎች አይደለም” በማለት በይፋ መናገራቸው የሚታወስ ነው። ይህንኑ ንግግራቸውን ጠቅሰው የተለያዩ ሚዲያዎች ዒላማው ፐሬዚዳንት ኢሳያስ እንደሆኑ ዘግበው ነበር።
ከላይ ፖለቲከኛው እንዳሉት የክልል ልዩ ኃይል ወደ መደበኛ የክልል አቅምነት እንዲወርድ፣ በየክልሉ ያሉ ራሳቸውን በመከላከያ ደረጃ ያስታጠቁ አገሪቱን ሊበትን የሚችል አዝማሚያ ስለሚያሳዩ በህገ መነግስቱ መሰረት እንዲበተኑ ሲወሰን ሻዕቢያ ቀድሞ በአማራ በኩል ጦርነት ያስለኮሰው የተድገሰለትን ስለሚያውቅ እንደሆነ ይታመናል።
አማራ ክልል የተጀመረው ጦርነት ባይኖር ኖሮ ሻዕቢያ ተረት እንደሚሆን የገባቸውና፣ መረጃው ያላቸው ካመለከቱ፣ ሻዕቢያ አማራ ክልል ያለውን ጦርነት ስለማቀጣጠሉ የሚሰጠውን መረጃ ያጥናክረዋል። ማተናከር ብቻ ሳይሆን መረጃዎችም አሉ። የመንግስት አንደበት የሆነው ፋናም ከብዙ ትዕግስት በሁዋላ በቅርቡ ሻዕቢያን ካረጀ የጋሪ ቸርኬ ጋር አመሳስሎ ቀጥቅጦታል። ይህ መንግስት ሻዕቢያ ላይ ያለውን አቋም ፍንትው አድርጎ ያሳየ ሆኗል።
የአማራ ክልል ጦርነት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች ከፕሪቶሪያው ስምምነት በሁዋላ የትህነግ አንድ ክፍል ከሻእቢያ ጋር መሞዳሞድ መጀመሩ ነበር። ይህ ግንኙነት “ሰሜኖች” በሚል አማራን የትግሉ አካል አድርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን መጣል ነው። ሆኖም ግን ትህነግ፣ ጫዕቢያና በተለይ ጎጃም ያለው የአማራ ኃይል አንድ ላይ ግንባር ሲገጥሙ “ጎንደርና ወልቃይት ጠገዴን ምን ለማድረግ ታስቦ ነው?| የሚል ስጋት ወዲያው አየሩን ሞላው። ይህንኑ ህብረት ለማጠናከር አዲስ አበባ ሆነው ሲጎነጕ የነበሩ፣ አዲስ አበባ ካለው የሻዕቢያ ኤምባሲ ከላላ ወስደው ከባህር ዳር እስከ ዱባይ ሲሰሩ የነበሩ ታወቀባቸው …. ይህ ወደፊት ይፋ የሚሆን ጉዳይ ነውና ለጊዜው “ወራጅ አለ” እላለሁ።
የሰሜን ኃይል ፈጥረው ወደ መሃል አገር ለማምራት ዕቅዱ ቢኖርም በአማራ ክልል የተጀመረው ጦርነት የተፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ ዱባይ የሚኖረው የሻዕቢያ በሳስ ይናገራል። ከዚህ በላይ ግን ኢሳያስ ትህነግን ሙሉ በሙሉ ማመን አልቻሉም። ትህነግ ቢመቻችለት እንደሚበቀላቸው ለአፍታም አይጠራጠሩም። ስጋቱ ከሳቸው አልፎ ህዝቡ ዘንድ እንዲወርድም አድርገዋል። ይህ ሁነታ ትህነግን ሁለት አሳብ ላይ እያነከሰ ጊዜ እንዲቆጥር አስገድዶታል።
መንግስትና ትህነግም ሊተማመኑ አለመቻላቸውን የሚገልጹ አሉ። ባለፈው በክህደት የተመታው የኢትዮጵያ መከላከያም በኤርትራ ድንበር ጀርባውን ለትህነግ ሰጥቶ መቀመጥ ዛሬ ላይ ይከብደዋል። አቶ ጌታቸው በግልጽ እንዳሉት 270 ሺህ ተዋጊ ሳይበተን ከነ ትጥቁ ቁጭ ብሏል። ይህ ኃይል ወደ መከላከያ የሚገባው በተሃድሶ መከላከያን እንዲቀላቀል፣ፖሊስ የሚሆነውም ፖሊስ ሆኖ የሚበተነውም እንዲበተን የተጀመረውን ሂደት አንዱ የትህነግ ቡድን አይደግፍም። ይህ አካሄድ ያዘለው ሌላ ጉዳይ ከማንም በላይ ለመንግስት ግልጽ በመሆኑ የቀደመውን ጥፋት እንዳይደግም ደጋግሞ እንዲያስብ አስገዳጅ ጉዳይ ነው።
ይህ እውነት ባለበትና መሰል ትዝብቶች በሚስተናገዱበት ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት ትግራይ እንዲገባና የኤርትራን ሰራዊት ከድንበር አካባቢዎች እንዲያርቅ፣ የያዛቸውንም 58 ቀበሌዎች እንዲያስለቀቅ ጥያቄ እየቀረበለት ያለው። ሰሞኑንን የቀድሞው ሌተናል ጄነራል ሳድቃን የተናገሩት ተጠቅሶ በሚዲያ እየተበተነ ያለውም ጉዳይ ይህ ነው።
በፕሪቶሪያ ግጭት ማስቆም እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሥምምነት “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ዓለምአቀፍ ድንበር ይጠብቃል። የኢትዮጵያ ሰራዊት በሃገሪቱ ድንበር ላይ ሰፍሮ የኢትዮጵያ ዜጎችን ደህንነት ይጠብቃል፤ የሃገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ያስከብራል፤ ከሌሎች ሃገራት የሚፈጸም ትንኮሳን ይመክታል” የሚለውን የስምምነቱን አንድ ክፍልም ይጠቅሳሉ። በተመሳሳይ ግን ህግ ተጠቅሶ የትግራይ ኃይል ከላይ በተባሉት አግባቦች ወደ ህግ ማዕቀፍ እንዲመለስ የሚገደድ ስለመሆኑ የሚባል ነገር የለም።
” ሻዕቢያ በባድመ እና በጉሎመኸዳ 58 ቀበሌዎች በህዝባችን ላይ ማንንነት ማስቀየርን ጨምሮ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍና በደል እየፈጸመ ነው። በፕሪቶሪያው ሥምምነት መሰረት ይሄን በደል የማስቆም ሃላፊነት የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊት ነው። እኛ ሰራዊቱ በትግራይ ክልል ገብቶ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ላይ መስፈር አለበት ያልነው በዚህ ምክንያት ነው” ሲሉ ፍትሃዊና ህጋዊ ጥያቄ የሚያነሱት ጻድቃን፣ መልሰው ይህ እንዳይሆን የሚከለክሉት ወገኖች እነማን እንደሆኑ ይገልጽሉ።
” እኛ በፕሪቶሪያው ሥምምነት መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወደ ትግራይ ገብቶ ሃላፊነቱን ይወጣ ማለታችን የሚያበሳጫቸው አካላት ሻዕቢያ በህዝባችን ላይ እየፈጸመው ያለው ግፍ የማይሰማቸው ይልቁንስ ለጠባብ ቡድናዊ ጥቅማቸው ከሻዕብያ ጋር በቅንጅት እየሰሩ ያሉ ሙሰኞች ናቸው።” ሲሉ ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገ/ትንሣኤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር ምክትል ፕሬዚዳንት በገሃድ ተናግረዋል።
ጻድቃን የህጉን አግባብ አስታወቁ እንጂ መንግስትን አልወቀሱም። ይልቁኑም ከሻዕቢያ ጋር የገጠሙ ቡድኖች መኖራቸውን ይፋ አድርገዋል። በዚህ መነሻ ውሳኔ ሰጪው የትግራይ ህዝብና ልሂቅ ነው። ድሮም ሆነ ዛሬ ከአገር መከላከያ ጋር የልብ ወዳጅነት ያለው የትግራይ ህዝብ አቋም ወስዶ፣ የትግራይ ታጣቂዎችን የሚመሩ መኮንኖች አንድ ውሳኔ ላይ ደርሰው ከመንግስት ጋር መተማመን ከፈጠሩ ሻዕቢያ እንኳን የኢትዮጵያን ድንበር ወሮ ሊያዝ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ፊት ለሰዓታት መቆየት እንደማይችል የባድሜው ጦርነት ምስክር ነው። ታሪክን ያቆሸሹ እንዳሉ ታሪክን የሚያድስ ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ሞገሷ የሚመልሰው ትግራይም በምታስነሳቸው ሃቀኛ አገር ወዳድና የወደፊቱን በሚያዩ ልጆች ጭምር እንደሆነ ይታመናል።
በዚህ መነሻ ለአገር መከላከያ የሚቀርበው ጥያቄ ምን ያህል ፍትሃዊ እንደሆነና እንዴት ሌተገበር እንደሚችል በቀናነት ማስላቱ ይበጃል። ማንም ይፈጽመው ማን ከቀድሞ ስህተት መማርም አግባብ ነው። ከምንም በላይ ህዝብ ላይ መቆመር ሊበቃ ይገባል። ህዝብም “በቃ” ሊል ግድ ነው።