“ሕገመንግሥቱ ከፌዴሬሽኑ መውጣት የፈለገ ካለ በሰላም እንዲሰናበት ያደርጋል” ብለው አለቆች ባስተማሩት መሰረት “ትግራይ ከፌዴሬሽኑ መቀጠል አልፈልግም” ስትል ይህንኑ ለምን ተግባራዊ አላደረገችም? የሚለው ነጥብ ነው። “ትግራይ ለምን ጦርነት ውስጥ ገባች? ምን ተፈልጎ ነው ወደ ጦርነት የተገባው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ የኬሪያ ኢብራሒም ብቻ ሳይሆን የበርካቶች ጥያቄ ነው።
የርዕዮት ሚዲያው ቴዎድሮስ በሌሎች ቃለ ምልልሶች አቅጣጫ ሰጪ ወይም leading questions በመጠየቅና ተጠያቂን ወደ ራሱ ፍላጎት በመጎተት ይታወቃል። በተለይም በጦርነቱ ወቅት ትህነግን በመቃወም አቋም ይዘው የነበሩ ሰዎች ወደ ሚዲያው ሲመጡ ማዋከብ፣ ማበሻቀጥና የመናገር ዕድል በመከልከል በደጋፊዎቹ ዘንዳ ማጠልሸት መለያው ነው። ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሒም ግን ይህ ዕጣ አልደረሳቸውም።
ኬሪያ ኢብራሄም ቴዎድሮስ በግልጽ የሚቃወማቸውን፣ በፍጹም ሊያስተናግዳቸው የማይመናቸውን ጉዳዮች አደባባይ አውጥተው ሲመሰክሩ እንኳን ሊያዋክባቸው፣ የመከራከሪያ ጥያቄ እንኳን ለማንሳት አልከጀለም። “ ጦርነቱን ብልጽግና ጀመረው፣ አብይ አሕመድ የትግራይን ሕዝብ ለመጨረስ አስቦ የጀመረው የጄኖሳይድ ወንጀል ነው” በሚል ቴዎድሮስ በፕሮግራሞቹ ሁሉ ደጋግሞ የሚያነሳውን አጀንዳ ኬሪያ “ ጦርነቱን መቅረት ይችል ነበር። አንድ ዓመት ብንታገስ ኖሮ ጦርነቱ አይነሳም ነበር” ሲሉ የስልታን ጥማት የጦርነቱ መነሻ እንደሆነ ገልጸዋል። መስክረዋል።
ለወ/ሮ ኬሪያ ጆሮውን ሰጥቶ በማዳመጥ ርዕዮት ሚዲያ ባሰራጨው ቃለ ምልልስ የተነሳው የህገ መንግስት ጉዳይ ለዚህ ጸሃፊ የፈጠራ ትርክትን የሚደመስስ “ትላቅ አጀንዳ” ነው።
ኬሪያ ኢብራሂም ህገ መንግስቱ “አልታደገንም”
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ “የምታወጣው ህግ ስልጣን ላይ እያለህ ሳይሆን፣ ስትወርድም ዋስትናና ከለላ መሆን አለበት” ይላሉ። ይህን ያሉት ስለ ህገ መንግስቱ ስልጣና ሲወስዱ በህገ መንግስቱ የተቀመጡት ቁልፍ አንቀጾች፣ አንቀጽ 39 “ካልተስማማን የምንለያይበት ነው” በሚል ነበር። እንደ እሳቸው ዕምነት ይህ ህገ መንግስት ትግራይን ከጦርነት አልታደጋትም። በዚሁ ሳቢያ ነው ትህነግ በስልጣን ዘመኑ ያወጣው ህግ ሲወርድ ሊታደገው ያልቻለው ወይም፣ አርቆ ማሰብ ያልቻለ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ያደረሳቸው። እንደ ወሰዱት ስጠና ለወይዘሮ ኬሪያ መገንጠል ለትግራይ ልክ እንደ አንድ ጥቅልል ስጦታ ዓይነት ነበር።
ትህነግ ወደ ትግራይ ጠቅልሎ በገዛ ፈቃዱ ከሄደ በሁዋላ ሲሰበኩ የነበሩ፣ ነገር ግን አፈጻጸሙ ያልገባቸው የዲፋክቶ ስቴት ነጠላ ዜማ እስኪታክተን አዚመዋል። አቶ ስብሃት ነጋ ከአውራ አምባው ዳዊት ጋር ባደረጉት ቆይታ “ማን እሺ ይልሃል? አብይ እሺ ይልሃል?” የሚል መስል ይሰጡ ነበር። ዳዊት የትግራይን ውለታ እየዘረዘረ የመገንጠል ጥያቄ ማስኬድ የሚቻልበትን አግባብ ሲያነሳ የአንቀጽ39 አባት “ የማይሆን ነው” ብለውት ነበር። ይህ እንግዲህ ገና አንድ ጥይት ሳይተኮስ የተላለፈ ሃቅ ነው።
ትህነግን የማይናበብ፣ የማይከባበር፣ የሚናናቅ፣ ስልታዊ እሳቤ የሌለው፣ አሻግሮ የማያይ፣ ወቅትን የማይገነዘብ፣ አቅሙን ያማያውቅ፣ ሌሎች የትም አይደርሱም፣ ምንም አያመጡም፣አይደፍሩንም ወዘተ እያለ በተራ መታበይ የሰመጠ ድርጅት እንደሆነ አመላክተው የዘለፉት ወ/ሮ ኬሪያ፣ አንቀጽ 39ን በመጥቀስ መለየት ያልተቻለበትን ምክንያት ዘርዝረዋል።
“የሁለቱም ምክር ቤቶች አወቃቀር ብዝሃነትን መሠረት ያደረገ ነው እንጂ ክልሎች ፌዴራሉን ተው፣ አትግፋን የሚሉበት አልነበረም፤ ሁለቱም ምክር ቤቶች ከብዙሃን ውክልና የተመሠረቱ ነበር፤ ይህ ደግሞ ትክክለኛ አይደለም” ሲሉ ሲነገራቸው የነበረው ሁሉ ተግብራዊ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ያመለከቱት ኬሪያ ኢብራሒም ይህን ስህተት የሰራው ድርጅታቸው እንደሆነ አስመረውበታል። ይህን ስህተት ተሽክሞ አንቀጽ 39 እያለ ሲፎክር መኖሩን ገልጸዋል። ይህን ያስረዱት ጦርነቱ እንዴት እንደተነሳ ለማስረዳት እንደ መነሻ ነው።
“50 ዓመት እንገዛለን፣ እንቆያለን በሚል የተሳሳተ ስሌት ህገ መንግስቱ ለፌደራል መንግስት ጡንቻ የሚሰጥ ሆኖ የተዘጋጀ በመሆኑ…” መገንጠል እንኳን ቢፈለግ ሊሆን እንደማይችል ኬሪያ በቃለ ምልልሱ ተናግረዋል። ጥያቄው ቢቀርብ እንኳ አስፈጻሚው ፌደራል መንግስትና ነጻ ሆነው ያልተደራጁ ተቋማቱ በመሆናቸው ጥያቄው ተቀባይነት ሊያገኝ እንደማይችል አብራርተዋል። ይህንኑ ጉዳይ በበላይነት የሚመራውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በበላይነት ያስተዳድሩ ስለነበር ሳንካውን በደንብ ስለሚረዱ ጠያቂያቸው ከማዳመጥ ውጭ የተነፈሰው አንዳችም ነገር አልነበረም።
“የመቶ ዓመት አጀንዳ ሰጥተናቸዋል” በሚል በገሃድ ከትህነግ ደጋፊዎች ይሰማ የነበረውን ትምክህት ወለድ ፉከራ ትክክለኛ መነሻ እንዳለው “ ለተበደሉ ሁሉ ድምጽ እንሆናለን” በሚለው በርዕዮት ሚዲያ በኩል ኬሪያ ኢብራሒም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ጉዳይ ” ሃምሳ ዓመት በስልጣን፣ ከዛ በሁውላ ስልጣኑን ስንለቅ ቀሪው የአገሪቱ ክፍል ሌላ ሃምሳ ዓመት የግጭት አጀንዳ ይሰጠዋል” ሲሉ የነበሩ ባልደረቦቻችን፣ በወቅቱ የቀልድ ያህል ቢያወሩም በነባር ታጋዮች የወጣው የአቶ መለስ ንግግር ግን የጉዳዩን ሚስጢር አጋልጧል።
ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ የተደረገበትን አግባብ አስመልክቶ የትህነግ ቁልፍ ሰዎች “መለስ ወደፊት አሰብን ከኢትዮጵያ ከመውሰድ ከሻዕቢያ መውሰድ ይቀላል። ለዚህ ነው የፈቀድነው” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ መስጠታቸውን አስታውቀዋል። በዚሁ ሂሳብ መሰረት ትህነግ 50 ዓመት ኢትዮጵያን ገዝቶ የሚፈልገውን ካገኘ ወይም እሚፈልገው ደረጃ ከደረሰ በሁውላ ስንበት ሲያሻው አሰብን ገቢ ያደርጉታል።
ይህን ስሌት ለክስረቱ ማሳያ ያነሱት ኬሪያ “እኔ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እያለሁ የሰራውት ውለታ የሚዘነጋ አይደለም” በሚል የሚቀርቡ የማንነትና የይገባኛል ጥያቄዎችን እንዴት ያስተናግዱ እንደነበር ያነሱት ኬሪያ፣ “ትግራይ መገንጠል ብትፈልግ የምታቀርበው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው” ሲሉ ልክ እሳቸው ሲያደርጉ እንደነበረው ዓይነት አያያዝ እንደሚገጥማቸው አመልክተዋል።
እዚህ ላይ ኬሪያ የተናገሩት ወይም ይፋ ያደረጉት ቁልፍ እና ወሳኝ ሃሳብ ቢኖር፤ “ሕገመንግሥቱ ከፌዴሬሽኑ መውጣት የፈለገ ካለ በሰላም እንዲሰናበት ያደርጋል” ብለው አለቆች ባስተማሩት መሰረት “ትግራይ ከፌዴሬሽኑ መቀጠል አልፈልግም” ስትል ይህንኑ ለምን ተግባራዊ አላደረገችም? የሚለው ነጥብ ነው።
“ትግራይ ለምን ጦርነት ውስጥ ገባች? ምን ተፈልጎ ነው ወደ ጦርነት የተገባው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አለመማግኘቱ የኬሪያ ኢብራሒም ብቻ ሳይሆን የበርካቶች ጥያቄ ነው። በተለይ በተደጋጋሚ ከተደረገው ጦርነት “ትግራይ ምን አተረፈች” የሚሉ ወገኖች የሚደጋግሙት ራስ ምታታቸው ነው።
“አንቀጽ 39 ተጠቅሶ መገላገል እንደሚቻል በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ የነበረ ድርጅት፣ ለዚሁ ህግ ጠበቃና ብቸና ሞግዚት ሆኖ የኖረ ፓርቲ ለምን ይህን ሁሉ ወጣት በነጻነት ሰበብ አስጨረሰ?” ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ለማይፈልጉና፣ ይህንኑ ጉዳይ ለሚያድበሰብሱ ኬሪያ “ አስቡና መልሱን ወዲህ በሉኝ” የሚል እንደምታ ያለው መረጃ ሰንዝረዋል። ጦርነቱን አስመልክቶ የትህነግ ጠበቃና ተከላካይ ሆኖ የዘለቀው ጠያቂያቸው ዝም ብሎ ተጨማሪ ማብራሪያ ሳይጠይቅ ያለፈው ይህ አንኳር ነጥብ ውሎ አድሮ አጀንዳ እንደሚሆን የሚታመነውም በዚህ መነሻ ነው።
ኬሪያ ኢብራሒም ህገ መንግስት ታከው ያነሱት የመወያያ አጀንዳ በደፈናው “ብልጽግና ወረርን” ሲሉ ለነበሩ፣ አሁንም ይህንኑ ለሚደጋግሙና ከደረሰው ጥፋት አንጻር ዛሬም በጥሞና ለመመርመር ፈቃደኛ ላልሆኑ ፈተና ነው። ምክንያቱም የትህነግ ስራ አስፈሳሚ ጦርነት ያስገባው ዋናው ጉዳይ የስልጣን ጥማት መሆኑን ገልጸዋልና።
ውስን አዛውንቶች የሚነዱት ትህነግ ለሌሎች አሳብ በር እንደሌለው በቁጭት ያስታወቁት ኬሪያ ኢብራሒም፣ ትግራይ ባይሳካም ምዕራብ ትግራይን ሳትከስር የመገንጠል ጥያቄ የማንሳት አማራጭ እያላት ወደ ጦርነት የገባችበት አገባብ አዛውንቶቹ ወደ ፌደራል ስልታን የመመለስ ፍላጎት ስላላቸው ብቻ ነው። ኬሪያ ቃል በቃል ባይሉትም “ የስልታን ጥማት ነው” በማለት ህገ መንግስቱ እንዳላዳናቸው ጠቅሰዋል።
ሻዕቢያ ሊያጠቃቸው ዝግጁ እንደነበር በትህነግ ስራ አስፈጻሚ ዘንዳ ሙሉ መረጃ እንደነበር ኬሪያ ተናግረዋል። ይህ ምስክርነታቸው ዛሬ ድረስ ሻዕቢያን መንግስት እንደጋበዘ አድርገው የፕሮፓጋንዳ ስራ ለሚሰሩት ሁሉ ራስ ምታት ነው። መከራከሪያ አልባ ሃቅም ነው። ምክንያቱም “ማን ያውራ የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” ነውና ነገሩ።
ኬሪያ ይህን ሲሉ አንዱና ዋናው የዚህ ትርክት አቀንቃኝ የሆነው ቴዎድሮስ አሳቡን አላነቀም። ሊከላከል አልሞከረም። አልሞገተም። አልተነፈሰምም። ምክንያቱም ቢነካካ ኬሪያ ብዙ ሊሉ ይችላሉና።
ለዚህ ማስረጃው “እስር ላይ እያሉ ሚስጢር ሰጥተዋል፣ወደ በረሃ አብረው አልወጡም” በሚል ቴዎድሮስ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች “ ወደ በረሃ ያልሄድኩት በራሴ ምክንያት ነው። አንዳንዴ የሚነገርም የማይነገርም ጉዳይ አለ” የሚል መልስ ከሰጡ በሁዋላ፤”አርሶ አደር ቤት መደበቅ ይህን ያህል ትልቅ ነገር አይደለም” ሲሉ አሽሟጠዋል።
ስለ ሚስጥር መሸጥ ሲመልሱ ጠያቂው እጅ በአፍ አስጭነውታል። “ ሁሉም መረጃ ነበራቸው” በማለት ብልጽግናዎች የመረጃ ችግር እንዳልነበረባቸው፣ በመኪና ሽሽት ሲደረግ የተዝረከረከ መረጃና በየቢሮው እንዳሻቸው መረጃ መሰብሰባቸውን በመጥቀስ ትህነግ በወቅቱ ሚስጢር ለመሰብሰብ የሚያስችል አቅም እንዳልነበረው በተዛዋሪ መልሰዋል።
ወ/ሮ ኬሪያ ሌላው ያነሱት ትልቁ ጉዳይ ምርጫ ነው። አንድ ዓመት መታገስ ቢቻል ጦርነቱ እንደሚቀር ገጸዋል። ቢያንስ ጊዜ መግዣ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ምርጫውን ዓመት ቆይቶ ማድረግ ቢቻል ኖሮ ፌደራል መንግስት እውቃና ይሰጥ እንደነበር ገልጸው ይህን ከማድረግ ይልቅ ጦርነት የተመረጠበትን አግባብ ኮንነዋል። ይህ ገለጻቸው አሁንም ጦርነቱን መንግስት እንደጀመረው ተደርጎ በተሰራው ትርክት ላይ ውሃ የሚከልስ ይሆናል።
“ትህነግ ከታች ሆኖ ሲታይ በጣም የሚያጓጓ ድርጅት ነው (እኔ ከታች ነው የተነሳሁት)፤ ሃሳባችን ልማትን እናፋጥን፣ ዴሞክራሲዊነትን እናሳድግ የሚል ይሆንና በተለይ ወደ መካከለኛና ከዚያም ከፍ እያልህ ወደ ከፍተኛ ከዚያም ወደ ማዕከላዊ ከዚያ ወደ ሥራ አስፈጻሚ ስትሄድ ግን ሁኔታው እየተቀያየረ ይሄዳል፤ ለሥልጣን ያለህ አተያይ ይለያያል፤ ለዱሮ ሕዝባዊና የዓላማ ጽናት የነበረው ድርጅት ለሥልጣንና ለጥቅሙ ሲሆን፣ ምንድነው? ይህንን ነውንዴ የፈለግነው? ትላለህ፤ ከታች በጣም እየጓጓህለት የመጣኸው ድርጅት ወደ ላይ ስትመጣ ግን በጣም የምትጠላው ድርጅት ይሆናል።” ሲሉ የገለጹት ድርጅታቸው “በተለይ አመራሩ እርስበርሱ የማይተማመን፣ የሚጠላላ፣ የማይከባበር፣ የማይደማመጥ፣ የሚናናቅ ሲሆን በጣም ነው የሚያምህ፤ ትክክለኛዋ ህወሃትና የትግራይ ሕዝብ የሚያውቃት ህወሃት ሌላ ነው” በማለት አሁን የተፈጠረውን ልዩነት ተንተርሶ ደርጅቱን እየተለዩ ያሉትን የማደራጀት፣ የመራትና አቅጣጫ የማሳየት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ መክረዋል። ከትግሉ እንደይሸሹም አመልክተዋል።
ነጻ አስተያየት ከአዲስ አበባ