“ስለየትኛውም አገር አንስቶ ለመተቸት ሞራልም ሆነ ስብዕና የላቸው” የሚባሉት የኤርትራ የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ የኦርሞን ሕዝብ ለይተው ለማስጠቃት ስም አበጅተው በጠላትነት ከፈረጁበት ቀን ጀምሮ በተቃዋሚዎችም ሆነ በመግስት ደጋፊዎች ዘንድ ያለ ምንም ልዩነት ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
“ኦሮሙማ” ኦሮሞነት መሆኑ እየታወቀ የክፉ ፖለቲካ እሳቤ በማድረግ በኩሽ ፓኬጅ ጠቅልለው ከሌላው የሰሜን አካባቢ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለማጋጨትና ለማጨፋጨፍ የጠመቁት ሴራ ከፍርሃት የመነጨ እንደሆነም ይገልጹ አሉ።
ኢትዮጵያ ህጋዊ ወደቧን የሸጡባት መሪዎች እንደነበሩ ሁሉ ህጋዊ ወደቧን ለማስመለስ የሚሰራ መንግስት መነሳቱ ያሳሰበው ሻዕቢያ አማራና ትግራይን በመያዝ “ሰሜኖቹ” ብሎ ኦሮሞን በጋራ ለማጥቃት የነደፈው ስሌት በራሱ ላይ ገመድ እንደመጠምጠም መሆኑን የሚገልጹ መረጃዎችም እየወጡ ነው።
ሻዕቢያ በዋና ስፖንሰሩ ግብጽ፣ የሱዳን ጦር መሪን፣ እንዲሁም እንዳሻው ይነዳዋል የሚባለውን ትህነግን፣ በቅርቡ የተወዳጀውን ውስን የፋኖ ኃይል በማቀናጀት በ”ኦሮሙማን እናጠፋለን” ሰም ኢትዮጵያን ለመበተን የተያዘውን ዕቅድ የመከላከያ ሚኒስትሯ ” አሳዛኝ፣ የማይሆን ተራ” ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን፣ ውጭ ጉዳይ በበኩሉ ” አፍ አልካፈትም” ማለቱ ይታወሳል።
ከዚህ ሁሉ በሁዋላ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሆርን አፍሪካ በኩል ሻዕቢያ ከያዛቸው የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ ዓለም ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
“የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እየጣሩ ነው፣ በሴም እና ኩሽ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች መካከል ጥላቻን በመፍጠር ውጥረት እና ግጭት እንዲፈጠር እየሰሩ ነው ሲሉ” አስተያየታቸውን የጻፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይህ አካሄድ ሊወገዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢሳያስ አፉወርቂ “ኢትዮጵያን እና ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ ለማተራመስ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስጠንቅቀዋል።
የሕዝብ እንደራሴና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የነበሩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሆርን ሪቪዩ በሚሰኘው የአገር ውስጥ ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት “የኢሳያስ አፈወርቂ የወቅቱ ፕሮጀክት ዋነኛ ትኩረት የአማራ እና የትግራይ ሚሊሻዎችን በማስተባበር እና በማቀናጀት የኢትዮጵያን የፌደራል መንግስት ለመጣል ነው” እንደሆነ አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አምባሳደር ዲና በጽሁፋቸው የኤርትራው ፕሬዝዳንት “የኦሮሞ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲጠላ ለማድረግ እየሞከሩ ነው” ሲሉ ከሰዋል። አምባሳደሩ ለዚህም ፕሬዝዳንቱ “ፍጹም ያልተረዱትን ፅንሰ ሀሳብ፣ ኦሮሙማን” በንግግራቸው ጠቅሰዋል ሲሉ ተችተዋል።
የፕሬዝዳንቱ ጣልቃ ገንብነት “በቃላት ብቻ የተገደበ አይደለም” ሲሉ የኮነኑት አምባሳደር ዲና “የኢትዮጵያ መንግስትን በትጥቅ ለመታገል የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያን ለማተራመስ በቀጥታ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አስገንዝበዋል። ይህ አካሄዳቸው “አስከፊ ውጤት ይኖረዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
“የኤርትራው ፕሬዝዳንት “ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲያስወጣ እና በኢትዮጵያ ትጥቅ አንስተው መንግስትን ለመውጋቲ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን ከመደገፍ እንዲቆጠብ ግፊት ልናደርግበት ይገባል” አስከፊ” ያሉት ውጤት ከመከሰቱ በፊት ፍትህና ሰላም ወዳዶች እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንቱ ኢሳያስ አፈወርቂ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በተከበረው የአገሪቱ 34ኛ ዓመት ነጻነት በዓል ላይ በጤና እክል ሳቢያ ባደረጉት የሃያ ደቂቃ ንግግራቸው ውስጥ ስድስቱ ደቂቃ ስለኢትዮጵያ ነበር። በዚሁ ንግግራቸው የኢትዮጵያን መንግስትን ክፉኛ ተችተዋል፤ ሕዝቡም በምሬት መሳቱን አወድሰው ተናግረዋል። ይህንኑ ንግግራቸው አድንቀውና አጉልተው በስም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ራሳቸውን በታጋይ ስም የሰየሙ የሚዲያ ባለቤቶች ሲያቀርቡትም ነበር።
ኢሳያስን አስመራ በመሄድ አብረዋቸው ሲሰሩ የነበሩትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ላይ የሰነዘሩትን ዘለፋ፣ በተለይም ኦሮሞነት ላይ አተኩረው ያሰራጩትን የማጥላላት ዘመቻ ያጎሉ ያሉትን ያህል፣ አምርረው የተቃወሙና ኢሳያስ እስካሉ ኢትዮጵያ ሰላም ሊኖራት አይችልም በሚል የደመደሙ በርካታ ናቸው።
ኢሳያስ በ1983 ከወያኔ ጋር አዲስ አበባ ሲገቡ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት፣ አየር ኃይልና ባህር ኃይል “የደርግ” በሚል ስያሜ እንዲፈርስ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሉት አሁን የተገነባውን ሰፊ የመከላከያ፣ አየር ኃይልና ባህር ኃይል ዳግም ለማፍረስ “የአብይ ጦር። የብልጽኛ ሰራዊት” በሚል በድጋሚ አፍርሶ አገሪቱን የጎበዝ አለቆች መፈንጫ ለማድረግ ዕቅድ በመያዝ ራሳቸውን ለዚህ ተግባር ከሸጡ ኢትዮጵያዊያን ጋር በትጋት እየሰሩ መሆናቸው በመረጃ መጋለጥ ከጀመረ ሰነባብቷል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “እነዚህ የታቀዱ ጦርነቶችን ለማስጀመር የጦር መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጅዎችን ለማግኘት የሚደረገው የግዢ ጥድፊያ፣ ተጓዳኝ ፉከራዎች እና ወታደራዊ ዝግጅት ሁሉም ያወቀው እና የመዘገበው ነው” በማለት እንቅስቃሴው ድብቅ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ኢሳያስ መንግስትን በኦሮሞነት ነጥለው በማውጣት፣ በመከፋፈል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያያዙትን የባህር በር አስፈላጊነት አጀንዳ “የሚያነሱት የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባህር፣ የባህር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ ነው” በማለት ሕዝብ የሚቆጭበትን የአሰብ ወደብ ባለቤትነት ጉዳይ አውድ በማሳት ለማቅረብ መሞከራቸው ነበር ከላይ በተጠቀሱት ወገኖች ያስደነቃቸው።
የኢትዮጵያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ኤርትራ ትርምስና ጦርነት እንደ ገቢ ምንጭ፤ “ኢሳያስን ሳይቃጠል በቅጠል” ተባለ፤ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ዛሬ! እርምጃ አሁን! ሲሉ አልጀዚራ ድረገጽ ላይ ሰፋ ያለ ዘገባ አሰራጭተው ነበር። “ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ በሁሉም ዋና ዋና ግጭቶች ውስጥ ተሳትፋለች እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ሊያባብስ በሚችል ድርጊት ተሰማርታለች” ሲሉ መውቀሳቸው ይታወሳል። እዚህ ላይ ያንብቡ To avoid another conflict in the Horn of Africa, now is the time to act