በኢትዮጵያ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ አሰራር መተግበር የሚያስችል የአምስት ዓመት ሀገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ፡፡
የአፍሪካ ህብረት የገጠር ልማት ዘርፍ፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን እና ሌሎች የመንግስት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በአፍሪካ ማዕቀፍ አገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁ ከመረጣቸው 12 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች፡፡
በዚህም መሰረት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ የሚከሰተውን በሽታ ለመቀነስና ሞትን ለመከላከል የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የገጠር ልማት ክፍል ሃላፊና የግብርናና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ተወካይ ዶክተር ጃኔት ኢደሜ እንዳሉት፤ በአፍሪካ በምግብ መመረዝ ምክንያት ለበሽታ የሚዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ የምግብ ደህንነት ስትራቴጂ ወሳኝ ነው፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት በየዓመቱ ከ200 በላይ ምግብ ወለድ በሽታዎች ይከሰታሉ ብለዋል፡፡
በአፍሪካ በየዓመቱ ከመቶ ሚሊየን በላይ ዜጎች ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ለበሽታ እንደሚጋለጡ ጠቅሰው፤ በዓለም ላይ በዚሁ ሳቢያ በየዓመቱ ከሚሞቱ 100 ሺህ ሰዎች መካከል ከ33 በመቶው በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በምግብ ወለድ በሽታ አማካኝነት ከሚሞቱ አፍሪካውያን መካከል 40 በመቶ የሚሆኑን ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት መሆናቸው ችግሩን አሳዛኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ እንዲፋጠን ከማገዝም ባለፈ አባል ሀገራት ከአፍሪካ የአፍላቶክሲን ቁጥጥር ህብረት ጋር በጋራ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ገቢራዊነት በገጠር ልማት፣ የውሃማ አካላትን ለዘላቂ ጥቅም በማዋል በምሳሌነት ትጠቀሳለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ቀድማ በማዘጋጀት ለጉዳዩ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ጀምራለች ብለዋል፡፡
በመሆኑም የአፍሪካ ህብረት እንደዚህ አይነት አህጉራዊ ጉዳዮችን በቁርጠኝነት ለሚተገብሩ አገራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቅድሚያ የምግብ ደህንነትን መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የምግብ ደህንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሁሉም ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ ላዘጋጀችው ሀገር አቀፍ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ትግበራ የሁሉንም የተቀናጀ ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ሀገር አቀፉ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረትና ያለችበትን ተጨባጭ ስራ የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የተቋማት ወጥ እና ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምግቦችን ፋብሪካዎች ላይ ብቻ በመቆጣጠር ደህንነታቸውን ማረጋገጥ እንደማይቻል ገልጸው፤ የምግብ ደህንነት ፍኖተ ካርታው ሁሉም በትብብር እንዲሰሩ ያግዛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ፤ በግብርናና ምግብ ምርቶች ላይ የሚከሰቱ የጤና ቀውስ የሚያስከትሉ ችግሮችን ለማስወገድ ከጅምሩ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከዘሩ ጀምሮ ለምግብነት እስከሚውሉበት ባለው የእሴት ሰንሰለት ደህንነቱን መጠበቅ ይገባል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የምግብ ደህንነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም