ሀሰተኛ መታወቂያና ስሞችን በመጠቀም የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን አውጥተው ግብይት ሳይኖር ደረሰኝ በመሸጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የተባሉ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ግለሰቦቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው ሀያ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመከራየት እና በሀሰተኛ መታወቂያ በወጣ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ግብይት ሳይኖር ግብይት ያለ በማስመሰል ደረሰኝ ሲሸጡ ነበር ተብሏል፡፡
ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ተጠርጣሪዎቹ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ለማውጣት በንግድ ስራ ላይ ያልተሰማሩና በአነስተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ ግለሰቦችን በገንዘብ አታለው እውነተኛ ስማቸውን እንዲቀይሩ በማግባባት የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽንን ጨምሮ የንግድ ምዝገባ ፍቃድ እና የንግድ ፈቃድ መለያ ቁጥር እንዲያወጡ አድርገዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከእነዚህ ግለሰቦች ውክልና በመውሰድ መመዝገቢያ ማሽኑ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ከሁለት አመት በላይ ደረሰኝ በመሸጥ ሲጠቀሙበት እንደነበር በምርመራ ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል ።
ፖሊስ ባደረገው ጥናትና ክትትል በወንጀሉ የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ሲሆን ለወንጀሉ መፈፀሚያ የሚጠቀሙባቸው የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽኖች፣ ኮምፒውተሮች ስካነር፣ ሃሰተኛ ማህተሞች፣ የእጅ በእጅ የሽያጭ ደረሰኝ እና ሌሎች የተለያዩ ሰነዶች መያዛቸው ተገልጿል ።
በተጭበረበረ መንገድ የሽያጭ ደረሰኝ ከህገ ወጦች በመግዛት ከመንግስት ገንዘብ ለማግኘት ተመሳሳይ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ አንዳንድ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ያለ ግብይት ደረሰኝ በመግዛትም ሆነ በመሸጥ ወንጀል የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቋል፡፡
(ኢ ፕ ድ)